Saturday, December 14, 2013

በጅዳ ቆንስል በር ውላ የምታድረው እህት ክራሞት…

Ethiopian woman in Saudi Arabia, Jiddah Ethiopian embassy ይህችን እህት በጅዳ ቆንስል መስሪያ ቤት በር ተቀምጣ  ለአንድ ሳምንት እንዳያት  ነቢዩ  ሲራክ የተባለው እና በዛው ከተማ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ይናገራል። አልፎ አልፎ  ሊያነጋግራት  ቢሞክርም መልስ አትሰጥም። መጀመሪያ ያያት ቀን አካባቢ ከስራ ለተፈናቀሉ እህቶች አነሰም በዛ መጠለያ እያለ ፣ ለምን በር ላይ ትሆናለች ብሎ የጠየቃቸው የቆንስሉ ጸጥታ አስከባሪ “አንተየ የዚህች እህት ጉዳይ አስቸጋሪ ነው ። ከመጠለያው ብዙ ቆይታለች ፣ አሁን በር ላይ የሆነችው ሃገር ቤት ለመሄድ ወረቀቷ አልቆ እያለ “ሃገር ቤት አልሄድም!” በማለቷ እነረደሆነ ነግረውታል ። “በመጠለያው የነበሩት ሰነዳቸው ባሳር በመከራ አልቆ ሲሸኙ ወደ ሃገር ቤት አልሸኝም ብላ ረብሻ ከማንሳት አልፎ ከተዘጋጀው መኪና ወርዳ ይህን የምታየው ሚኒባስ መስታውት ሰብራዋለች! ከዚያን ቀን ወዲህ አትበላም አትጠጣም ፣ እኛንም የገረመን ይሄ ነው። ምን ታደርጋለህ! ” ነበር ያሉት እኝህ የቆንስሉ ጸጥታ አስከባሪ ሲራክ ይህ ከተነገረው “ወዲህ ሃገር ቤት አልገባም!” ያለችው እህት ለቀናት በቆንስሉ በር  እንዳልጠፋች ይናገራል። ከተቀመጠችበት ወንበር ጀርባ ባለው ግድግዳ “ህጋዊ ሰነድ የሌላችሁ እና የወጣውን የሳውዲ ህግ መስፈርት የማታሟሉ ወደ ሃገር ግቡ !” የሚለው የቆንስል ማስታወቂያ ይታያል ። ከአጠገቧ በፕላስቲክ ኪስ የታጨቀ ጓዟን አስቀምጣ ፣ በሆዷ ቁርአን ታቅፋ አንገቷን ከመድፋት ባለፈ በአካባቢው አዛን ስትሰማ የዘወትር ጸሎቷን (ሰላቷን) ወንበሯን ፈቀቅ አድርጋ እንደምትሰግድ አንድ ዘወትር እንቅስቃሴዋን የሚከታተል የሲራክ ወዳጅ  አጫውቶታል… እንዲህ ሆና  ኩርምት ብላ ውላ ታድራለች! ቀን ጸሃይ ሲወቃት ፣ ማታ ወበቁ ይፈራረቅባታል። ሲራክ ካያት ቀን ጀምሮ ወደ መጠለያው እንድትገባ ከብዙ ሰዎች ጋር ሆነው ቢማጸኗትም  እንዳልተሳካላቸው  ነው የሚናገረው። ከሃገሯ በጤና የመጣችው እህት ችግር ውጋቷን እነሲራክ እንድታጋራቸው  ሲጠይቋት አትመልስም። ወደ ሃገር ቤት እንድትገባ በጅዳ ቆንስል ልትሸኝ ቢሞከርም አልተሳካም። የ”ሃገር ቤት ግቢ!” ” አልገባም!” አለ መግባባት ፍርሻ ከመምጣቱ በፊት አንዳንዴ ኦሮምኛና ብዙ ጊዜ ግን የተሰባበረ አረብኛ እየቀላቀለች መናገር ይቀናት እንደነበር አንድ “በመጠለያው እያለች  አውቃታለሁ።” ያሉ ወንድም ለሲራክ አጫውተውታል። ያን ሰሞን ወደ መጠለያው እንድትገባ ተለምና ብትገባም በመጠለያው ውስጥ ካሉ ግፉአን ጋር ግብ ግብ ፈጥራ መውጣቷን ይነገራል።
ይዚህች ግፉዕ እህት ሰላም የነሳና አዕሮዋን ያወከ የውስጥ ህመም ሚስጥር አይታወቅም። ትሰማለች ፣ ለመናገር አልፈቀደችም።  አንድም ቀን በር ላይ ውሎዋ ትንፍሽ ብላ ስትናገር ሲራክ እስከ ዛሬ እንዳልሰማት ይገልጻል። ውስጧ እንጅ ውጭ አካሏ የተጎዳ አይመስልም! ከሁሉም የሚገርመው ይህች እህት ጤናዋ ታውኮ እንኳ ሃገር ቤት ከወገኖቿ ጋር መቀላቀል ሞት መስሏታል።  ሲራክ  እንዲህ በማለት እይታውን ይደመድማል "ሌላው አስገራሚ ሂደት የዚህችን መልከ መልካም እጣ ፈንታ የምንመለከትም ህጋዊ ሰነድ የሌለን ብዙዎች የሳውዲን መንግስት የምህረት ቀቢጸ-ተስፋ ሰንቀን ጤናችን ተጠብቆ እያለ” በሰላም ሃገር ቤት ግቡ!” የሚለውን የመንግስትና የወገን ምክር መቀበል አቅቶናል! እንዴት ነው ነገሩ …?
አንድየ ይታረቀን ከማለት ባሻገር ምን ይባላል :) ብቻ እሱ ያቅልለው እንጅ የሚሰማ የሚታየው ይከብዳል ! … ያማል … ያማል!" በጣም ያማል። እናመሰግናለን ሲራክ ስላካፈልከን፡እባካችሁ የዝህችን ወገናችንን   ቤተሰብም ሆነ ዘመድ ወይም  የቅርብ ጓደኛ  የምታውቁ ካላችሁ ያለችበትን ሁኔታ በማሳወቅ ህይወቷ አስከፊ አደጋ ላይ ከመውደቁ በፊት ወገናዊ  ትብብራችሁ አይለየን።

No comments:

Post a Comment