Saturday, May 5, 2012

የጠቅላይ ምኒስትራችን ህልውና ሌላ የእኛ ህልውና ሌላ


ICT helps ensure our survival” Meles Zenawi 5th International on ICT for Development, Education and Training March 19, 2008
ከዚህ በላይ የተመለከተው ጥቅስ የተወሰደው የተከበሩት ጠቅላይ ምኒስትራችን በ 5ኛው ዓለምዓቀፍ የመረጃ ከምፒውተር እና ቴክኖሎጂ ስብሰባ ላይ እ᎐አ᎐አ᎐ በ2008 ዓ᎐ም᎐ ከተናገሩት የተወሰደ ሲሆን ግርድፍ ትርጉሙም እንደሚከተለው ነው "የመረጃና ከምፒውተር ቴክኖሎጂ ህልውናችንን እንድናረጋግጥ ይረዳናል"። ድንቅ አባባል ናት አይደል፦በዛን ዓመት "ህልውናችንን" ሲሉ የሰማ ኢቺ ውስጠ ወይራ ያልገባ ቋንቋ ያልገባው ሁሉ አቤት በቃ በአጭር ጊዜ ውስጥ እኝህ ምንም የማይሳናቸው መሪያችን ከዓለም ተርታ በ1ኛ ደረጃ አሰልፈውን  ህነትን፤ በሽታን፡ድንቁርናን፡ረሃብን፡ደህና ሰንብት ብለን የመኖር ዋስትናችንን የምናረጋግጥበት ዘመን እሩቅ እንደማይሆን ቢያልም አይፈረድበትም "ህልውናችንን ሲባል እነማንን እንደሚያመለክት ዛሬ ዛሬ ገሃድ እየሆነ መጥቷል። ለዚህም ይመስላል የተከበሩና የተወደዱ ጠቅላይ ምኒስትራችንና የስራ ባልደረቦቻቸው በከፍተኛ ደረጃ ከወጭ የሚያገኙትን ብድር/እርዳታ እና ከሃገር ውስጥ ከግብር ከፋዩ የሚሰበስቡትን በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ዜጎችን በተለያየ መንገድ
ለመሰለል (በሃገር ውስጥና ውጪ)፡የተለያዩ የዜና፡የብሎግ እና ሌሎች መሰል ድረ ገጾችን ለማገድ፡በስልክ የምናደርገውን እያንዳንዷን ንግግር እና መልእክት ለመጥለፍ ወዘተ ቀን ከሌሊት የሚዳክሩት፡፡ ይሄ ሁሉ እንግዲህ "ህልውናችንን" ለማረጋገጥ ነው። ይሄን ሁሉ ድካማቸውን ግን ማንም ከቁጥር ያስገባላቸው የለም፡ይሄ ምስጋና ቢስ ዓለም። ኢትዮጵያ እ᎐አ᎐አ᎐ በ 2012 ዓ᎐ም᎐ በመረጃ ፍሰት ቴክኖሎጂ በዓለም ላይ ከሚገኙ 142 ሃገሮች ውስጥ በ130ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡እድሜ ለ ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት (ብመደአበእንግሊዝኛው ምህጻረ ቃል NISS (National Intelligence and Security Service) የሚባለውን መስሪያቤትና በቅርቡ የተቋቋመውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤወይም በእንግሊዝኛው (Information Network Security Agency (INSA - ኢንሳ) እንዲሁም ቻይና ይሄንንስ ማን አየበት።  በዚህ ዓመት ጥር ላይ ይመረቃል የተባለውስ የመረጃ እና ቴክኒዎሎጂ ፓርክ ጉዳይስ ከምን ደረጃ እንደደረሰ የሚያውቅ ካለ እስኪ አለሁ ይበል።ይሄን ሁሉ የጠቅላይ ምኒስትራችንን ልፋት ዋጋ ለማሳጣት ካልሆነ እንዴት አገራችን ውስጥ ያለው የኢንተርኔት እና የተንቀሳቃሽ ስልክ ስርጭት መጠን መንግስት አልባ ከሆነችው ሶማልያ በታች ሊሆን ቻለ የሚለው እጅግ በጣም ያሳዝናል። ይሄንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ይመስላል  በእንግሊዝኛው ምህጻረ ቃል NISS  (National Intelligence and Security Service) በመባል የሚታወቀው የስለላ መ/ቤት በድርጅታዊ አወቃቀር፣ በሰው ኃይል፣ በቴክኒክ ብቃት፣ በገንዘብ ወዘተ በኢትዮጵያ ካሉት መ/ቤቶች በላቀ ደረጃ ላይ እንዲገኝ ጥረት የተደረገው፡፡ ይህ በህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ቁጥጥር ሥር የሚገኝ መ/ቤት አገዛዙ ለሥልጣኑ የሚያሰጉትን በሙሉ በማደን፣ በማሰስና በቁጥጥር ሥር በማዋል በአጠቃላይ ለህወሃት ህልውና ስጋት የሆነን ሁሉ ከመንገድ የሚያስወግድ ኃይል ነው፡፡
ይህ ድርጅት እንደ ማንኛውም ተቋም የራሱ የሆነ ድክመት ቢኖሩትም (በተለይም የቴክኖሎጂ እሴቶችን ከመጠቀም አኳያ) በከፍተኛ ፍጥነት እየተሻሻለና ፈጣን ለውጦችን እያካሄደ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡ ተጠያቂነትን በተመለከተ ግን የህወሃት የቀኝ እጅ እንደ መሆኑና የቀድሞውን የህወሃት የደኅንነት መምሪያ የተካ ስለመሆኑ አሁን የሚከተለው አሠራሩ በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡ ስለሆነም ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ወይም ለይስሙላ ለሚሠየመው ፓርላማ ሳይሆን በቀጥታ ለመለስ ዜናዊ መሆኑ እንዲሁም በተቋሙ ውስጥ በቋሚ ሠራተኛነት የሚያገለግሉትና ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነው የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው የዚህ መ/ቤት ዋነኛ መለያዎች ናቸው፡፡
 አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሰሃራ በታች በሚገኙ አንዳንድ ጎረቤት አገሮች ማለትም እንደ ኬንያ፡ዩጋንዳ እና ታንዜንያ የሚኖሩ አፍሪካውያን ወገኖቻችን ከጊዜ ወደ ጊዜ መንግስቶቻቸው ባደረጉዋቸው ጥረቶች አማካይነት ኢንተርኔትን እና ተንቀሳቃሽ ስልክን ለተለያዩ አገልግሎቶች እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ። ከነዚህም መካከል የብድር፡ሃዋላ፡የባንክ፡የግብይት ገበሬዎች ስለምርቶቻቸው ብሄራዊ/ዓለማቀፋዊ ዋጋ የሚያውቁባቸው መንገዶች በመፈጠሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ የኢንተርኔትና የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል። እኛም ጠቅላይ ምኒስትራችን ህልውናችንን ሲሉ ይሄን መስሎን ነበር። እንዴ ስልካችን ቢጠለፍ፡የምንላላካቸው መልእክቶች ቢሰለሉ እኮ ለእኛው ህልውናና ደህንነት ተብሎ ስለሆነ ቅር ሊለን አይገባም። እስቲ አስቡት አንድ ወለጋ ወይም ጎጃም ገጠር መንደር ውስጥ የሚኖር ገበሬ የላቡ ውጤት ስለሆነው የምርቱ ዋጋ ቤቱ ቁጭ ብሎ አዲስአበባ ወይም ሌላ ከተማ ከሚኖር ነጋዴ ጋር ሲደራደር፡ ይሄንን ነበር ያለምነው ጠቅላይምኒስትራችን ህልውናችን ሲሉ። አስቧት ዝዋይ ወይም ነገሌ ቦረና የምትኖር ያለ አባት ልጆቿን ለማሳደግ አሳሯን የምታይ እናት በተንቀሳቃሽ ስልክ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ሆና በጎች በማርባት እና የራሷን እና የልጆቿን ህይወት ስታሻሻል ይሄንን ነበር ያለምነው ጠቅላይምኒስትራችን ህልውናችን ሲሉ። የጠቅላይምኒስትራችን ህልውና እና የእኛ ህልውና ለየቅል እንደሆኑ ከዚህ በላይ መረጃ አያስፈልግም። ለነገሩ የእነሙባረክንና ቤን አሊን አወዳደቅ ያየ በኢንተርኔት አይጫወትም። አምባገነኖች የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡ኢንተርኔት ደግሞ ዋነኛ ጠላታቸው ነው፡ለጊዜው ዜጎችን በተለያየ መንገድ በማፈን ጊዜ መግዛት ይቻል እንደሆን እንጂ ከማይቀረው ማእበል አያድንም። 

No comments:

Post a Comment