እንዴት ከረማችሁ?
ያለፈው ሳምንት እንዴት ነበር የእናንተን እንጃ የኔ ግን ለየት ያለ ነበር? ከባድ ሃዘን ላይ ነኝ መቼም በተከበሩ ጠቅላይ ምንስትራችን ላይ የወረደውን መከራ ያየ አገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ በሙሉ (ይሄ እነዚህ በአውሮፖ እና አሜሪካ የጠቅላይ ምኒስትራችንን እግር እየተከተሉ ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉ ጸረ ልማት እና ዲሞክራሲ ተቃዋሚዎችን አይመለከትም) ቢያንስ ቢያንስ ሰባት ቀን እንዳገራችን ባህል ፍራሽ መሬት አውርዶ በመተኛት፡ከል በመልበስ የአገራችንን በምግብ ራሳችንን የመቻል ስኬት ልምድ ለመጋራት በሄዱበት ወቅት ክብርና ዝናቸው በአንድ አሸባሪ ጋዜጠኛ አማሪካን አገር ውስጥ መገፈፉን በመቃወም ልማታዊ ሃዘኑን መግለጽ አለበት።
ታሪኩ እጅግ አሳዛኝ ስለሆነ ጽሁፉን ማንበብ ከመጀመራችሁ በፊት ባጠገባችሁ የጨርቅ ወይም ወረቀት እንባ ማበሻ ብታዘጋጁ የሚመረጥ ሲሆን አኬልዳማ ድራማን እንዲያዩ ያልተፈቀደላቸው ህጻናትም ባካባቢው ባይኖሩ ተመራጭ ነው። በሉ እንግዲህ ተዘጋጁ። በመጀመሪያ ከዚህ በታች ያለውን ጥቅስ ልተርጉምና ወደ ዝርዝሩ የሃዘን ዜና እገባለሁ። የሚከተለውን ጥቅስ የተወሰደው አምባገነኖችን ማሸነፍ፦በአፍሪካና በመላው የሚገኙ አምባገነኖችን መታገያ ከተባለው በእውቁ የጋና ኢኮኖሚስት ፕሮፌሰር ጂዮርጅ አዬቴ ከተጻፈው መጽሃፍ ሲሆን ጥሬ ትርጉሙም እንደሚከተለው ነው። እጅግ የተከበረ አምባገነን መሪ የለም፧ ጥሩ አምባገነን መሪ የሞተው ብቻ ነው። “There is no benevolent dictator. The only good dictator is a dead dictator”.*





