Monday, September 16, 2013

ዝዋይ እስር ቤትን ያየ ቃሊቲን ያመሰግናል።

እውን የነጭም የጥቁርም ደም ለኢህአዴግ አንድ ዓይነት ነው?
እንደምን ከረማችሁ? እንኳን ወደ አዲሱ ዓመት "በሰላም" (መቼም አንዳቾቻችሁ ምን ሰላም አለና እንደምትሉ መጠርጠር ግድ ይላል፡ እኔም ከእናንተ መሃል አንዱ ነኝ) ተሸጋገራችሁ። 2006 እንዴት ይዟችኋል? ግን ግን እንደው ግርም አይልም የእኝህ የ"አዲሱ" ጠቅላይ ምኒስትር ነገር። ትዝ ይላችሁ እንደሆን ሟቹ ጠቅላይ ምኒስትር ከመሞታቸው በፊት ሁለቱን ስዊድናውያን ጋዜጠኞች ለመፍታት ሃሳብ እንዳላቸው ጥያቄ ቀርቦላቸው "በህግ ፊት ሁላችንም እኩል ነን (ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ አለች የምትለው ጥቅስ ትዝ አትላችሁም) ጥቁርም ሆነ ነጭ ደማችን አንድ ነው" ብለው መልስ ሰጥተው ነበር። በኋላ ላይ ግን ቀኝ አዙር ብለው ለፈረንጆቹ
ከመሞታቸው በፊት "ምህረት" በማድረጋቸው በ 2005 መባቻ ላይ ተፈተው አገራቸው በመግባት ይህንኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሳለፉትን አስደሳች እና አስደናቂ ተሞክሮ በመጽሃፍ መልክ በማሳታተም  በዚህ እለት ለህዝብ ይፋ ያደረጉ ሲሆን እስክንድር ነጋ፡ ርዕዮት ዓለሙ፡ ውብሸት ታዬ እና ሌሎች በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የህሊና እስረኞች ያሉበት አስከፊ ሁኔታ ውይይት ተደርጎበታል። እናም እዚሁ ዝግጅት ላይ የቀድሞው አዲስነገር ጋዜጣ አዘጋጅ የነበረው እና በሌለበት በአሸባሪነት ወንጀል ተከሶ 8 ዓመት ተፈርዶበት እዚህ ስዊድን አገር በስደት የሚኖረው ጋዜጠኛው መስፍን ነጋሽ ተገኝቶ እነዚህ የቀደሞ የሙያ አጋሮቹ ስላሉበት ሁኔታ ከጓደኞቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ያገኛቸውን መረጃዎች አካፍሎናል። ልብ በሉ እንግዲህ እኝህ "አዲሱ" ጠቅላያችን የቀድሞውን እና የታላቁን መሪያችንን ራዕይ ሳይበረዝ ሳይከለስ አስፈጽማለሁ ሲሉ ብዙ ጊዜ የተደመጡ ሲሆን ታዲያ ምን ሆነው ነው ውብሸት ታዬ ያስገባውን የይቅርታ ደብዳቤ ያልተቀበሉት፡ወይስ የነጭ ደም ከጥቁር ይበልጣል?
ውብሸት ታዬ ከዝዋይ እስርቤት ምድራዊ ሲዖሉን ቃሊቲን ለምን ናፈቀ? 
ርዕዮት ዓለሙስ ባልሰራችው ወንጀል ታስራ መንገላታቷ ሳያንስ በሙስና ወንጀል ተከሰው ዘብጥያ የወረዱት የቀድሞ ህውሃት ቱባ እና ነባር ተጋዳላይቲ ኮሎኔል ሃይማኖት ዛቻ እና ስድብ እንድትቀበል የተደረገው በማን ትዕዛዝ ይሆን? ሂድ አትበለው እንዲሄድ አድርገው ካልሆነ በስተቀር እነዚህ ንጹሃን ወገኖቻችን በህገወጥ መንገድ መታሰራቸው ሳያንስ ከቤተሰቦቻቸው፡ከዘመዶቻቸው፡ከጓደኞቻቸው እንዲሁም ከሌሎች ጎብኚዎቻቸው ጋር እንዳይገናኙ የታገዱትስ በየትኛው የህግ አግባብ ነው? መቼም ታስሬስ ጠይቃችሁኛል የሚለውን የቅዱስ መጽሃፍ ትዕዛዝ ለመፈጸም አዲሱ ጠቅላያችን ካለባቸው የስራ ብዛት እንደማይችሉ ብንገምትም እንዲህ መረን ያጣ፡ኢሰብዓዊ ህገወጥ እና ኢሞራላዊ ድርጊቶች በንጹሃን ዜጎች ላይ የእስርቤት ሃላፊዎች እና ባለጊዜ ታሳሪዎች ሲፈጽም ሰምቶ እንዳልሰማ፡አይቶ እንዳላየ መሆን ከአንድ ወንጌላዊ መሪ እና የሁለት ልጆች አባት የሚጠበቅ ነውን? ለማንኛውም ካሎት ጊዜ ሁለት ደቂቃ ብቻ ሰውተው ከዚህ በታች ለምን ውብሸት ታዬ  ከዝዋይ እስርቤት ይልቅ ለምን ቃሊቲን እንደመረጠ እስኪ የሚከተለውን ቪድዮ ይመልከቱና ፍርድዎን ይስጡ። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ማናቸውም እስርቤቶች በምን አይነት ዘግናኝ ሁኔታ እንዳሉ የአደባባይ ምስጢር ነው፡ ይሄንን ደግሞ የትም መሄድ ሳያሻን ሁለቱ ስዊድናውያን ጋዜጠኞችና የቀድሞ እስረኞችዎ   438 ቀናት

በሚል ርዕስ ባለፈው ቅዳሜ ለህዝብ ይፋ ከሆነው መጽሃፋቸው በቃሊቲ ስላሳለፉት ገሃነማዊ ህይወት ምን ይመስል እንደነበር ለመገንዘብ ይቻላል። ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራሩጧል ቢባልም፡ ውብሸት ይሄንን ሲዖላዊ እስርቤት የመረጠበት ምክንያት በምቾቱ ወይም በሌላ ምክንያት ሳይሆን ከጨቅላ ልጁ እና እንደልብ ለመንቀሳቀስ ከማይችሉት አቅመደካማ እና አረጋዊ ወላጆቹ ጋር "እንደልብ" ለመገናኘት ብቻ ነው። ክቡር ጠቅላያችን ዛሬ ጠዋት እርስዎ ሁለቱ ልጆችዎን ቁርስ አብልተው ግምባራቸውን ስመው ወደ ትምህርትቤት ከላኩዋቸው በኋላ ወደስራ እንደሄዱ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ባለፈው ዓመት ከአንድ ድረ ገጽ ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ላይ ከዛሬ 22 ዓመታት በፊት ለከፍተኛ ትምህርት ከሄዱበት ፊላንድ ወደ ኢትዮጵያ አንዱ ለመመለስ የፈለጉበት ምክንያት በወቅቱ የሁለት ዓመት እድሜ የነበራት የመጀመሪያ ልጅዎ ዮዋና እንደነበረች ተናግረዋል። ግንግን፡ 135ኪሜ ርቀት ላይ በእስር የሚማቅቀው ውብሸት ታዬ እንኳን ልጁን ቁርስ ሊያበላ ቀርቶ ካለው የቦታ ርቀት እና በልጁ  እድሜ አነስተኝነት ምክንያት ዓይኑን የሚያየው በሁለት ወር አንድ ጊዜ ብቻ ነው። መቼም ለእርሶ ስለልጅ ፍቅር ማውራት ለቀባሪው አረዱት ያሰኛል። እናም እባክዎን የያዙትን ስልጣን በመጠቀም በ 2006 ዓም ለዚህ መረን ላጣ ግፍ ገደብ ያብጁለት። እስኪ ከማብቃቴ በፊት ግን እርስዎና ባልደረባዎችዎ ያጸደቁትና እናከብረዋለን የሚሉት ነገር ግን በመላው አገሪቱ በሚገኙ የእስርቤት ዋርዲያዎች እንደፈለጋቸው የሚሸራርፉትን የኢትዮጵያ ህገመንግስት አንቀጽ 21 በጥበቃ ስር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብት ምን እንደሚል ላስታውስዎ እና በዚሁ እንለያይ። መልካም አዲስ ዓመት ከነመላው ከሚወዷቸው እና ሁልጊዜም ከማይለይዎት ውድ ልጆችዎ እና ቤተሰብዎ ጋር።

አንቀጽ 21 በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብት

1. በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት አላቸው፡፡
2. ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሃይማኖት አማካሪዎቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቸው ጋር ለመገናኘትና እንዲጐበቿቸውም ዕድል የማግኘት መብት አላቸው፡፡ 


No comments:

Post a Comment