Monday, December 2, 2013

በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ህይወታችን አደጋ አንዣቦበታል ይላሉ

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ( ኢሳት )ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ ያነጋገራቸው ወገኖች እና አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ በሳውዲ የሚኖር ጋዜጠኛ በሳውዲ አረቢያ የሚታየው ሁኔታ እጅግ አስፈሪ ነው ይላሉ። ከ40 ሺ በላይ ኢትዮጵያን በእስር ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ። ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚፈልጉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቀናቸውን ይጠባባቃሉ። የኢትዮጵያ መንግስት በመቶ ሺ የሚቆጠረውን ስደተኛ ለማስተናገድ የመደበው የሰው ሀይል 40 ብቻ ነው። የሳውድ አረቢያ መንግስት ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ ኢትዮጵያውያን ከአገሪቱ ምድር ተጠራርገው እንዲወጡ እየቀሰቀሰ ነው። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ አደጋ ሊፈጠር ይችላል ብሏል አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ ጋዜጠኛ።
አርብ እለት  በተለያዩ የሳውዲ ከተሞች በተንቀሳቃሽ ስልክ የተበተነው አጭር መልዕክት ህጋዊ ለተባሉትም ሆነ ህገወጥ ለሚባሉት ኢትዮጵያውያን የማስጠንቀቂያ ደወል ነው ይላሉ እኝህ ጋዜጠኛ።
የተበተነው የተንቀሳቃሽ ስልክ አጭር መልዕክት ኢትዮጵያውያንን ቀጥራችሁ የምታሰሩ እንዲሁም መኖሪያ ቤት ያከራያችሁ ሁሉ በአስቸኳይ እንድታስወጡ፣ ይህን ባታደርጉ ግን
100 ሺ ረያል ትከፍላለችሁ የሚል እንደሆነ ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል። ይህን መልእክት ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከተከራዩበት ቤት ተባረዋል። 9 ኢትዮጵያውያንን ወደ አስጠጋው ኢትዮጵያዊ በመደወል መታሰቢያ ቀጸላ አነጋግራቸዋለች። እርሱ እንደሚለው መልክቱ መተላለፉን ተከትሎ ጓደኞቹ ከቤታቸው እንዲወጡ ተደርጎ በእርሱ ቤት ተጠልለዋል
ከቤታቸው ከተባረሩት መካከል አንዱ ከ8 ወራት በፊት አባቱ ቤታቸውን ሸጠው ፣ በኪራይ ቤት እየኖሩ በህጋዊ መንገድ እንደላኩት ይናገራል። አሁን ቤትክን ለቀህ ውጣ ተብሎ ህይወቱ አደጋ ላይ ወድቋል
የሳውዲ መንግስት በይፋ እንዲህ አይነት መልክት ያስተላልፍ እንደሆነ የጠየቅነው ጋዜጠኛ፣ መንግስት በቀጥታ እንዲህ አያደርግም ነገር ግን እርሱ ባሰማራቸው ሰዎች አማካኝነት መልክቶችን እንደሚሰድ ይታወቃል ብሎአል።
የኢትዮጵያ መንግስት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ዘመቻ በማድረግ በመቶሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ህይወት መታደግ ሲችል በቀን ይህን ያክል ሰው አስመጣሁ በማለት ፕሮፓጋንዳ ይነዛል የሚለው ጋዜጠኛው፣ በሳውዲ የቀረው ኢትዮጵያዊ ወደ አገር ቤት የተመለሰውን በብዙ እጥፍ ይበልጣል ሲል በአገሪቱ ያለውን እውነታ አስረድቷል።
በሌላ በኩል ከሳውድ አረቢያ ወደ የመን የገቡ 3 ሺ ያክል ኢትዮጵያውያን በምግብ እጥረት ተጎሳቁለው እንደሚገኙ እስር ቤት ድረስ በመሄድ ጋዜጠኛ ግሩም ተክለሀይማኖት ጎብኝቷቸዋል።


No comments:

Post a Comment