Friday, November 1, 2013

ልብን የሚሰብረው የሰርካለም ፋሲል ደብዳቤ ቃሊቲ እስር ቤት ለሚገኘው ለባለቤቷ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ

እንደመግቢያ
ዛሬ ጠዋት ነበር ይሄን አንጀት የሚያላውስ በሰርካለም ፋሲል የተጻፈውን ራሷ በድምጿ ያነበበችውን ደብዳብዳቤ ያዳመጥኩት። ኧቤት ግፍ፡ኧቤት መከራ? የእነዚህ ሁለት ኢትዮጵያውያን ወገኖች እና እስርቤት የተወለደው ልጃቸው ናፍቆት ወንጀል ምን ይሆን? የሰርካለምን ትረካ እያዳመጥኩ እምባዬ መቆጣጠር አልቻልኩም። እንደ ሰው በወጉ ተሳስመው፡ ተቃቅፈው፡ ተላቅሰው አይደለም የተለያዩት፡፡ በአጥር ሽቦ ተለያይተው፡ማዶ እና ማዶ እየተያዩ፡ ጣታቸውን አነካክተው ናፍቆታቸውን እና ስንብታቸውን በስርዓት ሳይወጡ በደቂቃዎች በሚለካ ንግግር ነበር። ከሁሉም የሚደንቀው እና ብርታት የሚሰጠው ግን የሰርካለም መንፈሰ ጠንካራነት እና በዚህ አስቸጋሪ እና ፈታኝ ሁኔታ ላይ ሆና ነገን በተስፋ ሰንቃ ባለቤቷን እና አብረውት ባልሰሩት ወንጀል በእስር የሚሰቃዩትን የሙያ አጋሮቹንና ሌሎች በሺህ የሚቆጠሩ ንጹሃን ኢትዮጵያውያን የህሊና እሰረኞች ተስፋ እንዳይቆርጡ የሚገልጸው ጠንካራ ያለው መልዕክት መላኳ ነው። ኢትዮጵያ ሃገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የገደለሽ በልቶ የሞተልሽ ተላ።
አዎ የገደለሽ በላ፡ ይቺ ዓለም ዝብርቅርቅ በተለይማ የእኛዋ ኢትዮጵያ  ከሁለት ዓመት በፊት ህይወቴ አደጋ ላይ ነው፡ልታሰር ነው፡ልፈለጥ ነው ብሎ ከአገር ኮብልሎ
በአሜሪካን አገር ጥገኝነት ጠይቆ የነበረው ጋዜጠኛ ዛሬ ቁጭ ብሎ ሲያስበው በወቅቱ የወሰደው ውሳኔ ትክክል እንዳልነበረና የመጻፍና የመናገር ነጻነትን ለማስከበር በሚደረገው ትግል ለመታገል በመወሰን ወደ እናት አገሩ መመለሱን ሰምተናል። እቺ ናት ጨዋታ፡ እቺ ናት ኩመካ።
እስክንድ ነጋን በቅርበት አላውቀውም። ከእግዜር ሰላምታ የዘለቀ ተነጋግረን አናውቅም።  ት ዝ ይለኛል ኢትዮጵያ ጋዜጠኛ ሆኘ በምሰራበት ጊዜ ኢሲኤ ወይም የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሺን በሚገኘው ለጋዜጠኞች በተዘጋጀው የኢንተርኔት ማእከል (በወቅቱ ፈጣን የሚባል ኢንተርኔት አላቸው ከሚባሉት ድርጅቶች አንዱ እሱ ነበር) እስክንድር ይመጣ ነበር፡ በጣም ጠዋት ወይም ከሰዓት። ሁላችንንም ሰላም ካለ ትንሽ ከፊሊሞን ጋር ከተቀላለዱ በኋላ ወንበሩን ይዞ ማተም የሚፈልገውን ነገር ካተመ በኋላ ሌላውን ደግሞ ከኮፕምፒውተሩ ላይ በፍሎፒ ዲስክ (ለመሆኑ ፍሎፒ ዲስክ አሁንም አለ) ላይ ከገለበጠ በኋላ በመጣበት ፍጥነት ወደ ስራው ይመለሳል። እንደሌሎቻችን እዛ ተጥዶ አይውልም ነበር። ዛሬ አንድ በጣም የሚቆጨኝ ነገር ከእስክንድር ጋር በደንብ ቁጭ ብዬ ለማውራት አለመቻሌ ነው። አንድ ቀን እድል ቀንቶኝ እንደማገኝው ተስፋ አለኝ። አይዞህ ወንድሜ የጨለመው ቀን ይበራል፡ አሳሪዎች ህም በሰፈሩት ቁና ይሰፈራሉ።
በሉ ብዙ ዝባዝንኬ አላብዛባችሁ። ደብዳቤውን ቃል በቃል የጻፍኩት፡ የመስማት ችግር ላለባቸው ሰዎች የደብዳቤውን መልእክት እንዲረዱት በማሰብ ነው።

ይህችን አጭር ደብዳቤ ስሞነጫጭር በአይነህሊናዬ ፊትለፊት ቆሞ የሚታየኝን እስክንድርን በማሰብ ነው። ከሃገር ከቤተሰብ ከጓደኞቼ ከራቅኩኝ ሶስት ወር አለፈኝ እስክንድርንም ካየሁት እንዲሁ። እነዚህን ቀናቶች እንዴት እንዳሳለፍኳቸው መዘርዘሩ አሰልቺ ስለሆነ ትቼዋለሁ። ከእስክንድር ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ስንብት። እለተ ማክሰኞ ሃምሌ ፩፮ /፳፻፭ ጠዋት፤ በዚህች እለት ማታ እኔ እና ልጄ ቦሌ ኤርፖርት መገኝት አለብን ስለዚህ ፩፪ ሰአት ከመድረሱ በፊት ብዙ አጣዳፊ ስራዎች ይጠብቁኛል፤ አስቸጋሪውና ፈታኙ የ፩፰ አመት ፍርደኛውን ቃሊቲ እስርቤት ሄዶ መሰናበት ነበር። ደባሪ ቀን የቀን ጎዶሎ ብሎ ማለት ይሄ አይደል። አሳቤ ብትንትን ብሏል። የእስክንድርን አይን እያዩ ቻው ነገ አልመጣም ተነገወዲያም ኧረ የዛሬ ወርም የዛሬ አመትም ብሎ መለያየት እንዴት ይከብዳል??? የተጎዳን ስሜት የትኛው አረፍተነገር በትክክል ይገልጽዋል??? ምናልባት እንባ። እኛስ መንገደኞች ነን። ወዲህ ወዲያ ስንል ሃሳባችን ይበታተናል። ያ በትንሽ አጥር ውስጥ ካላሽንኮቭ በታጠቁ ወታደሮች የተከበበው ጀግና ስንሰናበተው ምን ይሰማዋል? ይችለው ይሆን?  እንዴት ስ ይቋቋመዋል?  ከራሴ ጋር አወራለሁ። ምንድነው የምንባባለው ቃላት እመርጣለሁ "ደህና ሰንብት አሜሪካ ልንሄድ ነው፤ስትፈታ እንገናኛለን" ልበለው ወይስ "አይዞህ፤ በርታ፤ ቻል አድርገው፤ ሁሉንም እንዳመጣጡ ተቋቋመው፤ አይ ከጎንህ ብሆን ጥሩ ነበር ግን ለመሄድ ጨከንን"። ሁሉም አያስደስትም። ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም ይላል ያገሬ ሰው።  እኔ እና ልጄ ከቤት የወጣነው ጠዋት አንድ ሰዐት ነው፤የመጨረሻ ጉዞ፣ ቃሊቲ እስርቤት ለስንብት ግና ቀጥታ ወደ ቃሊቲ አላመራንም። ለእስክንድር የሚያስፈልጉትን እቃዎች ከመንገድ መገዛዛት ጀመርኩ። "ምን ነበር የሚያምረው?" አውቀዋለሁ። "ምን ነበር የሚያስፈልገው?" እገዛለሁ። አሁን የምገዛዛውን ከሳምንት በፊት እንደገዛሁለት ባውቀውም የመጨረሻዋ እለት ደግሞ መደጋገም ጀመርኩ። ኩርቱ ፌስታሌን ሞላዃዋት።እቺ ኩርቱ ፌስታል የእስረኛ ሻንጣ ናት።  ሰዐቴን ተመለከትኩ አራት ሰዐት ያንተ ያለህ ከምኔው በረረ ምን ያሮጥሃል?ከግኡዝ ነገር ጋር ንትርክ፤ ለእኔ ሲል ቶሎቶሎ የሚሮጥ መሰለኝ፤ ማንስ ወደኋላ ይጠምዝዘው?ወደፊት ብቻ። አራት ሰዐት ከሰላሳዐምስት አካባቢ ቃሊቲ ደረስኩ። እዚያ ደግሞ ወረፋ፤ የመከራ ለሊት ቶሎ አይነጋም ይባል የለ። ሰልፉ ደቂቃዎችን ተሻማኝ። ጎበዝ እንዲህ ነው መፈታተን፤ ንድድ ቅጥል ጭርጭር ብቻዬን፤  አይደርስ የለ ዞን ሁለት እስረኞች በሚጠየቁበት ስፍራ ላይ እገኛለሁ።  ስም የሚጣራው እስረኛ ከመላመዳችን የተነሳ በደንብ ተዋውቀናል። ገና ሲያየኝ በድምጽ ማጉያው "እስክንድር ነጋ፤ እስክንድር ነጋ" ሲል ተጣራ።  ፈራሁ ከሁለት እና ከሶስት ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ብቅ አለ በፈገግታ ታጅቦ። ቀረበ፤ ለመጨባበጥ እጃችንን ዘረጋን፤ ግና እንዴት? በመካከላችን ሰፊ የሽቦ አጥር አለ።  በሽቦ መካከል እንደምንም ሁለት ጣቴን አሾለኩኝ። እሱም እንደዛው። ተጨባበጥን ወይስ ተነካካን? እንዴት ናችሁ? ሁለታችንንም ጠየቀን። "ናፍቆት እስኪ አዋራኝ። በኋላ አሜሪካ ልትሄድ ነው። አይዞህ እሺ እወድሃለሁ" ለልጁ ይናገራል። ከልጁ ጋር እየተነጋገረ በመሃል "እኔን አይዞሽ ጠንክሪ፤ ስለእኔ ምንም ሃሳብ እንዳይገባሽ" ወደልጁ ይቀጥላል። "ናፍቆት ጎበዝ ተማሪ ሁን፤ አባባ ደስ እንዲለው አንተ በደንብ መማር አለብህ። ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋለህ?" "መኪና ነጂ፤ ሾፌር"  አለው ናፍቆት።     እስክንድር ሳቅ አለና "እንግዲያውስ ሹፌር የሚኮነው ጎበዝ ተማሪ ስትሆን ብቻ ነው። ጎበዝ ከሆንክ መኪና ትነዳለህ"። ያቋርጣል "እሺ ሰርካለም ከእስሬ በላይ የከበደኝ የእናንተ ነገር ነበር። ዛሬ እፎይ የምልበት ቀን ነው። ይህንን ስልሽ ጥላቻ እንዳይመስልብኝ፤ ከፊቴ እንድትርቁም ብዬ አይደለም። ቅጣቴን
ብቻዬን መቀበል ስላለብኝ ብቻ ነው። አንቺ አንኳን ታውቂዋለሽ። ግን ልጄ ሰባት ዐመት ሞልቶታል፤ ክፉና ደጉን መለየት ጀመሯል። ውስጡ ጥላቻ ይዞ እንዲያድግ አልፈልግም። ልጄን ለአንዲት ቀን ከፊቴ ባላጣው ደስ ይለኝ ነበር፤ ራስ ወዳድ መሆን ግን አልፈልግም። ይሄ ለእኔ ከባድ ውሳኔ ነው። ናፍቆት እስኪ አዋራኝ"፤ ሁለት ሰው ማጽናናት እንዴት ይከብዳል? ስሜቱ እንዳይታወቅ አንዴ ከእኔ አንዴ ከልጁ፤ አሳዘነኝ እስክንድር። ይሄን ሲናገር ዐይኑ ደም እየመሰለ ነበር። እስክንድር ልታለቅስ ነው እንዴ አልኩት፤ የራሴ እምባ እየተናነቀኝ።  ኧረ በፍጹም እንዴት አለቅሳለሁ?መልሶ ጠየቀኝ። ዐይንህ በጣም ቀላ። በእጁ ዐይኑን አሸት አሸት አደረገና እኔ እንግዲህ ባጭር ጊዜ ከእስር አልወጣም፤እንደምታውቂው ይቅርታም አልጠይቅም፤ የሰራሁት ወንጀል ስለሌለ። ስለዚህ የፈጀውን ጊዜ ቢፈጅ እታሰራለሁ፤ ይህ እምነቴ ነው፤ደግሞ ወደ ልጁ ናፍቆት "በጣም እወድሃለሁ"።  ኧቤት ግራ መጋባት፤ ይሄን ሁሉ እንዲሆን ምክንያት የሆነውን ጨካኝ መንግስት ረገምኩት። ጉድጓዱን አርቀህ አትቆፍረው የሚገባበት አይታወቅምና። እስክንድር እዳህን እየተወጣኸው ነው ለሃገርህ ለህዝብህ መከፈል ያለበትን ዋጋ እየከፈልክ ነው። ውስጥህ ሰላም አለ፤ያልተበረዘ ያልተከለሰ። እምነት አላማ ጽናት።  ያንተን እድል ብዙሃኑ አያገኘውም። ኩራ ባለህበት። ጀግና ነህ፤ ጀግንነት በጦር ሜዳ ውሎ ብቻ አይለካም። ለእኔ ጀግነት በዓላማ መጽናት ነው፤ ጀግንነት ፈተናውን ማለፍ ነው፤ ጀግንነት ግዳጅን መወጣት ነው፤ ጀግንነት ውስጥህን ማዳመጥ ነው፤ ጀግንነት ሆኖ መገኘት ነው። ወሪያችን አላለቀም። የመጨረሻ ቃሌ፤ እስክንድር ጠንክር፤ የልጅህ የልጄም አደራ አለብኝ። አቅሜ እስከቻለ እናትም አባትም ሆኜ አሳድገዋለሁ አታስብ።
አልጨረስኩም፤ ይህቺ ክፉ ሰዐት ትሮጣለች አላልኳችሁም? አጥር ተመታ፤ በቃችሁ፤ የፖሊሱ ድምጽ። "ግባ በቃህ!" ተለያየን። ይህችን ጽሁፍ የምጽፋት፤ በሶስተኛ ወሬ ነው። ጥቅምት ፩፮ ፪፻፮ በሃገርኛ የቀን አቆጣጠር ማለት ነው። ማታ ስምንት ሰዓት ከሰላሳዓምስት በሃገርኛ ሰዓት።    በአሮጌ ሞባይሌ ላይ የተሞላችው የኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር አሁንም አለች። እለት ተእለት ባትሪዋን በመሙላት እንዳትጠፋብኝ እከታተላታለሁ። ለምን ይሆን? እኔእንጃ። ይቺ ክፉ አይሮፕላን ለምን ይዛንመጣች ነው ያለው ልጄ። የመለያየታችንን ዋዜማ ሳነሳው፤ የእስራቱም ዋዜማ ታወሰን። መስከረም ፩፡፪፻፬ ቅዱስ ዮሃንስ ዘመን መለወጫ። ብሩህ ያልሆነ ቀን በጠዋቱ የጨፈገገ፤ በዓል በዓል የማይሸት፤ ክብድ የሚል፤ደባሪ፤ስንቱን አወረድኩበት።  ይሄ ለእኛ ቤት ብቻ ነው። በዓሉን በቤታችን ለማከበር ብዙም ተነሳሽነት አልነበረንም እኔንም እስክንድርም። በተለይ የእስክንድርን ትኩረት የሳበው በወቅቱ በአረብ ሃገራት እየተካሄደ ያለው ሰላማዊ ተቃውሞ ነበር። በየደቂቃው አዳዲስ ክስተት ስለሚሰማ የበዓሉ እለት ጠዋት እስክንድር ላፕቶፑ ላይ አፍጥጧል። ከመረጃ ቋፉ ላይ የሚያነበው አዳዲስ ነገር እያነበበ ይነግረኛል። "ጋዳፊ ተሰወረ፤ጋዳፊ ተከበበ"።  በዓሉን እንደምንም በዓል ለማስመሰል ተፍጨረጨርን። አሪፍ ግን አልነበረም። ፭ ሰዓት ሲሆን ቤታችንን ቆልፈን ወጣን። እስክንድር መኪና ያሽከረክራል፤እኔና ልጄ ከኋላ ተቀምጠናል። ቦሌ አካባቢ አንድ ካፌ ጎራ አልን። የበዓል ቀን ካፌ እና ሬስቶራንት ጭር ይላል። ወደ ምሽት ካልሆነ ቀን ብዙም ሰው አይጎበኛቸውም ምናልባት እንደኛ የተጫጫነው ካልሆነ። ካፌው ጭር ብሏል፤ ናፍቆት ሚሪንዳ፤እኔ ኮካ እስክንድር ቡና አዘዝን። ከቤታችን የበለጠ ልንዝናናበት የገባንበት ቤት ጨለማ ነበረ። ብዙም ሳንቆይ ሂሳባችንን ከፍለን ቤቱን ለቀቅን። መንገዱ ጭር ብሏል፤ መኪኖች አልፎ አልፎ ነው የሚታዩት። እስክንድር፤
"ዛሬ የማሳይሽን ቦታ ልብ ብለሽ እይው የልጆች መዝናኛ ነው ናፍቆትን እየመጣሽ አጫውችው"
አላስጨረስኩትም፤ "እኔ ልጅ ማዝናናት ትዕግስቱ የለኝም፤ ራሽ አምጣው፤ አንተ ምን ስለሆንክ ነው እኔ የማዝናናው እኔ እዚህ ቦታ አልመጣም"። እስክንድር ሃይለቃል አይናገርም፤ ቁጡም አይደለም። ረጋ ብሎ "እኔ ከሌለሁ ብዬ ነው"። አሁንም አላስጨረስኩትም "የት ልትሄድ ነው?" "አይ ዘንድሮን አታልፋትም ዋጋህን ታገኛለህ እያሉ በስልክም በኢሜይልም እየዛቱብኝ ነው። ስለዚህ ላዘጋጅሽ ብዬ ነው"።  "በበዓል ይሄ አይወራም አሁንም አቋረጥኩት"። አንዴ ስለጠመምኩ መቃናት አቃተኝ
ጠማማ አስተሳሰብ። "እወቂው ብዬ ነው" ብሎ ጸጥ አለ። አሳዘነኝ። አለመረበሹ ደግሞ ጽናት ሆነኝ። ይህን ሊያሰማኝ ነው በዓሉ የደበዘዘብኝ? በዚህ ይለፍ። ግን አላለፈም፤ ከአንድ ቀን በኋላ መዓት ይዞ መጣ። ብሶት የወለዳቸው የጊዜ ጀግኖች ዛቻቸውን ወደ ተግባር አሸጋገሩት፤ ኦሮማይ። ዛሬ ሁለት ዓመት ከሁለት ወሩ።      እኔ እና ልጄ አሜሪካ፤ እስክንድር ደግሞ ቃሊቲ ይገኛል። የእኔ አሜሪካ መቆየት የእስክንድር ቃሊቲ መሰቃየትእስከመቼ ነው ለሚለው መልስ የለኝም። ላደለው አገርን የመሰለ ነገር የለም። ካገሩ የወጣ ሰው ለእኔ ሙሉ አይደለም፤ አንድ የሚጎለውን ነገር ተሸክሞ ይዞራል። ሁልጊዜ እርካታ የለውም። እዚህ ላይ እስክንድርን እንደመነሻ አቀረብኩት እንጂ እንደ አንዷለም እምቢ ለነጻነቴ ርዕዮትን የመሰለች ጠንካራ፤ጽናት፤ብርታት፤የሚደርስባትን ግፍ ተቋቁማ ነገን የምታልም፤ ናቲ እውነተኛ የሃገር ፍቅር የሚታይብህ አቤ በራስ መተማመንን፤ ውብሸት አይዞህ ጨለማው ይገፈፋል። ሁላችሁም ያልጠቀስኳችሁ በአሁኑ ሰዓት ጨለማው ዓለም ውስጥ ያላችሁ፤ ነገ ፍንትው ያለች ብርሃን ትወጣለች እና አይዞአችሁ በርቱ።
መስከረም ፳፩/፳፻፮አሌክሳንድሪያ ቨርጂኒያ። ሰርካለም ፋሲል።

No comments:

Post a Comment