Tuesday, November 19, 2013

ህውሃት በሪያድ የሚገኘውን ቆንስላ በመዝጋት በሺህ የሚቆጠሩ በሳውዲ የሚገኙ ወገኖቻችንን ለአስከፊ አደጋ አጋለጠ

ውሻ በበላበት ይጮሃል
 
እንደሚታወቀው ኑሯቸውን ለማሻሻል በሚል ከአፍሪካ እና ከእስያ የተውጣጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በየዓመቱ በህጋዊ እና ኢህጋዊ በሆኑ መንገዶች ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት በተለይም ሳውዲ አረቢያ ባህር አቋርጠው፡ድንበር ተሻግረው አየር ሰንጥቀው ጉዟቸውን በየእለቱ ያቀናሉ። ይህ በእንዲ እንዳለ፡ የሳውዲ መንግስት ፖሊስ እና ወጣት ወንዶች ኢትዮጵያውያን ላይ ያነጣጠረውን መጠነ ሰፊ፡ዘግናኝ እና ኢሰብዓዊ ወንጀል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በማጠናከር እና በማስፋፋት ላይ እንደሚገኙ ከሰሞኑ ከዚያች አገር በተለያየ መንገድ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። እህቶቻችንና እናቶቻችን ይደፈራሉ ወንድሞቻችን ይገደላሉ፡በአደባባይ ይደበደባሉ ሌሎች ደግሞ በእነዚህ ጋጠወጥ ጎረምሶች ታፍነው ወደ አልታወቀ ቦታ ተወስደው ለከፋ ስቃይ እና እንግልት ተዳርገዋል። ይህ በሳውዲ ዜጎች ያስቆጣው ርህሩህ ልማታዊ መንግስታን ደግሞ የረባ አገልግሎት ሰጥቶ የማያውቀውንና በዚች ቀውጢ ጊዜ እነዚህን ወገኖች ለመታደግ ባለፈው እሁድ በሪያድ የሚገኘውን ቆንስላ ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱን አስታውቋል። እነዚህ ወገኖቻችን ሳውዲ ውስጥ ለመቆየትም ሆነ ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚያስፈጓቸው የመጓጓዣ ሰነዶች የሌላቸው ሲሆኑ የቆንስላው መዘጋት ህይወታቸው ከመቼውም በበለጠ ለከፋ አደጋ እና ችግር ተዳርጓል። እንዲህ ነው እንግዲህ ለወገን ተቆርቋሪ እና አሳቢ መንግስት፡ ዛሬ በሺህ የሚቆጠሩ ልጆቻችን፡እህቶቻችን፡እናቶቻችን፡ወንድሞቻችን፡ እና አባቶቻችን ህይወት በእነዚህ ጨካኝ፡ አረመኔ እና ለሰው ልጅ ህይወት ደንታ በማይሰጣቸው የሳውዲ ፖሊሶች እና ጎረምሶች ቁጥጥር ስር የሚገኝ ሲሆን አራት ኪሎ ምንይልክ ቤተመንግስት የሚገኙት ገዥዎቻችን ጭራሽ ይባስ ብለው የሳውዲ መንግስት በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደረገውን ዘመቻ ከማሞካሸት አልፈው አገርቤት ይህ ድርጊት ያስቆጣቸው እና የእነዚህን የተቸገሩ ወገኖቻችንን ድምጽ ለማሰማት ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ንጹህ ኢትዮጵያውያንን
በመደብደብ እና በማሰር ማንነታቸውን አስመስክረዋል። ይህ አገር ክህደት ካልተባለ፣ምን ሊባል እንደሚችል አላውቅም፡ ምንዓልባት ጩኅቴን                    ቀሙኝ ወይስ ውሻ በበላበት ይጮሃል? ምርጫውን ለእናንተ ትቻለሁ። ከዚህ በታች በሚገኘው ቪድዮ ላይ እህቶቻችን የድረሱልን፡
የወገን ያለህ፡የመንግስት ያለህ ጥሪ በማሰማት ከእነዚህ ሳውዲ ውስጥ ባልታወቀ ቦታ ከአገቷቸው በኋላ እንደፈለጉ ከሚጫወቱባቸው እና ወንድሞቻቸውን ዓይናቸው እያየ ከገደሉት ሃያ የሳውዲ አውሬዎች  እንድንገላግላቸው በሚጮሁበት እና በጭንቅ በሚሰቃዩበት ወቅት፡  ከዚህ አሰቃቂ እና ዘግናኝ ድርጊት በመጠኑም ቢሆን ሊገላግላቸው የሚችለውን ቆንስላ መዝጋት፡ የህውሃት መንግስትን ማንነት እና 
ምንነት በትክክል አጉልቶ ያሳያል።  እንኳን ህዝብ እና መንግስት (መንግስት አለ ከተባለ) አደራ ተጥሎበት የዜጎችን መብት እና ክብር ለማስጠበቅ የተላከ ዲፕሎማት ይቅርና ማንም ጤነኛ አእምሮ ያለው ተራ ግለሰብ እንዲህ አይነቱን አሳፋሪ ወንጀል በወገኖቹ ላይ በዚህች የቁርጥ ቀን አይፈጽምም።

ልማታዊ ዲፕሎማቶች

ህውሃት መራሹ እና አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘውን ጸሃዩ መንግስታችን መቼም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ  ለምንገኝ ዜጎቹ ደህንነት እና ክብር በመቆርቆር እና በማሰብ ማንም የሚያህለው የለም። በቅርቡ ከስልጣን የተሰናበቱት መሪያችን ባለፈው ዓመት ከሳውዲ መንግስት ጋር 45 ሺህ ኢትዮጵያውያትን (ይህ እነዛን ከወርቃማው ዘር የተፈጠሩትን አይጨምርም) በየወሩ በቤት ሰራተኝነት ለመላክ ውል ፈርመው መመለሳቸው ምን ያህል ለእነዚህ ንጽሃን ኢትዮጵያውያት ያላቸውን ፍቅር እና አክብሮት ያሳያል። የህውሃት ደግነት እና ርህሩህነት በዚህ ብቻ አያበቃም የቤተሰቦቸቻውን ፍቅር ህጻናት በውጭ አገራት ለሚገኙ ወላጆች በከፍተኛ ዋጋ በማደጎነት በመቸብቸብ፡ እነዚህ ህጻናት በእነዚህ ማንነታቸው በማይታወቅ ግለሰቦች እጅ ለርሃብ፡ጥማት፡ለስቃይ እንዲያም ሲል ለሞት እንዲዳረጉ በማድረግ መንግስታዊ ሃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል። ከዚህ ባለፈ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ዜጎች ለዘመናት ከትውልድ ትውልድ ተወራርሶ ሲጠቀሙበት የነበረውን ሰፊ መጠን ያለው ለም መሬት፡ወንዝ፡ሸንተረር እና ደኖች ከኤስያ እና ሳውዲ ለመጡ ባለሃብቶች በርካሽ ዋጋ በማከራየት ኢትዮጵያውያኑ ከቤት ንብረታችው እንዲፈናቀሉ ሲደረጉ ባለሃብቶቹ ደግሞ ሩዝ እና ሌሎች ምርቶችን በማምረት የየአገሮቻቸውን በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የዜጎቻቸውን የምግብ ፍጆታ በማሟላት ላይ ይገኛሉ። እድሜ ለህውሃት፡ ኢኮኖሚያችን 11 በመቶ እያደገ ሲሆን ሰብዓዊ መብትና የህግ የበላይነት አንበሽብሾናል። ለዚህ ይመስላል በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሱዳን፡በሶማሌ፡በየመን፡በሰሃራ በረሃ እንዲሁም አስቸጋሪውን የሜዲቲራኒያን እና የቀይ ባህሮችን በማቋረጥ ህይወታቸውን ለአደጋ የሚያጋልጡት። ከፊሉ በሰሃራ በረሃዎች እና ከሞዛምቢክ እስከ ደቡብ አፍሪካ በሚገኙ ጫካዎች የአሞራ እና የአውሬ ሲሳይ ሲሆን፡የተቀሩት ደግሞ ህይወታቸውን ባህር ላይ አጥተዋል። ከእነዚህ የተረፉት ደግሞ በየመን እና ግብጽ በረሃዎች ወስጥ በሚገኙ ህገወጥ ደላሎች ለባርነት፡ለስቃይ፡ለረሃብ፡አስገድዶ መድፈር እና እንዲያም ሲል ለሞት እየተዳረጉ እንደሆነ ያረጀ ያፈጀ ዜና ከመሆን አልፎ እንደተራ ነገር እየተቆጠረ ይገኛል። ይህን ሁሉ መከራ እና ስቃይ አልፈው ሳውዲ ወይም ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገራት እግራቸው የረገጠ እህቶቻችን እና ወንድሞቻችን እጣ ፋንታ በእነዚህ ቦታዎች በሚገኙ ቀጣሪዎች፡ደላሎች፡የጸጥታ ሃይሎች እና ተራ ዜጎች ቁጥጥር ስር ነው። ማንም የፈለገውን በፈለገው ጊዜ እና ቦታ በእነዚህ በተረሱ እና በተጣሉ ወገኖቻችን ላይ የሚያደርግ ሲሆን የነዚህን ዜጎች መብት፡ክብር እና ድህንነት ለማስጠበቅ በሚል በግብር ከፋይ  በሚንቀሳቀሱት ኤምበሲዎችም ሆነ ቆንስላዎች ውስጥ የሚሰሩት ተወካዮች በተለያየ መንገድ ተገድለው የሚመጡ የኢትዮጵያውያን አስከሬኖችን ከመገነዝ እና የራሳቸውን ህይወት ከማደላደል ውጭ አንዳች ፋይዳ ያለው ነገር ሲሰሩ አልታዩም። እቺ ናት ልማታዊ ዲፕሎማቶች።   


No comments:

Post a Comment