Thursday, April 26, 2012

የኢትዮጵያውያን የተቋውሞ ሰልፍ በስቶክሆልም ፳፻፬ ዓ/ም

በስዊድን አገር የሚኖሩ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ሚያዚያ ፩፯/፳፻፬ ዓ/ም ከቀኑ ከሰባት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት በኢትዮጵያ ቆንስል ፊት፡ለፊት በመገኘት የኢህአዴግ መንግስት እያካሄደ ያለውን በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ዜጎችን ከሚኖሩበት ቀዬ የማፈናቀል ዘመቻ፡ በሃይማኖቶች ጣልቃ ገብነት፡ በስመ ልማት የመሬት ቅርጫ፡ እንዲሁም ሴቶችንና ህጻናትን ለዘመናዊ ባርነት የመዳረግ ወንጀሎችን እንዲያቆም ተቋውሟቸውን አሰሙ። ከዚህም በተጨማሪም በቃሊቲና በሌሎች እስርቤቶች በመማቀቅ ላይ የሚገኙ የህሊና እስረኞች ባስቸኳይ እንዲፈቱ፡ የህግ የበላይነት እንዲከበር፡ የዜጎች የመናገር፡የመጻፍ፡የመሰብሰብና በነጻ የማሰብ መብቶች እንዲከበሩ የስራ ማቆም አድማ ላይ በተሳተፉ መምህራን ላይ የሚካሄደውን መዋከብ የመለስ ዜናዊ መንግስት ባስቸኳይ እንዲያቆምና ስልጣኑን በህዝብ ለተመረጠ መንግስት እንዲያስረክብ አሳስበዋል። ተሰላፊዎቹ የኢትዮጵያን ሰንደቅ በማውለብለብ እና ልዩ ልዩ ቀስቃሽና ወቅታዊ መፈክሮችንና መዝሙሮችን ካሰሙ በኋላ በመጨረሻም የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪዎች እነዚህ በዓለምዓቀፍ ህግ የተደነገጉ ሰብዓዊና የዜግነት መብቶች በኢትዮጵያ እንዲከበሩ የሚያሳስቡ ጥያቄዎቻቸውን በደብዳቤ መልክ ለቆንስላው ተወካይ በማቅረብ የተቋውሞ ሰልፉ ተጠናቋል።

No comments:

Post a Comment