Sunday, April 22, 2012

ከፈላ ያስከፍላል ፍዳ

ከኢትዮጵያ ወጥታ አረብ አገር የገባች ነፍስ
ፍዳ ትበላለች ተጠፍራ እንዳጋሰስ
ይቅርታ ለተወለጋገደችው ስንኝ  ተብዬ። ችግር በቂቤ ያስበላል ትል ነበር እማዬ ነፍሷ በሰላም ይረፍና ቂቤ እንዲህ አልማዝ መሆኑን ሳታይ በግዜ ተገላገለች እንጃ አሁን ተረቱ ተለውጦ ከሆነ እንዴ መቼም እነንትና ካልሆኑማ ማንም በቂቤ የሚተርትም/የሚቀልድም ያለ  አይመስለኝም። 
ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ልመለስ፦መቼም አብዛኛዎቻችሁ ይሄንን ከዚህ በታች የሚገኘውን በሳውዲ በሚገኙ ኢትዮጵውያውያን እህቶቻችን/ልጆቻችን የሚደረገውንና እንኳን በሰው ልጆች ላይ በእንስሳት ላይ መፈጸም የሌለበትን ጨካኝ፡ኢሰብዓዊ እና ዘግናኝ ድርጊት የሚያሳይ ፊልም ሳታዩ አትቀሩም ወይም የወሬ ወሬ የሰማችሁ ይመስለኛል። ይሄ ፊልም የሚያሳያው በአንድ የሳውዲ አረቢያ ከተማ ውስጥ በኢትዮጵውያን ሴቶች ወገኖቻችን ላይ ስለሚፈጸመው ግፍ ሲሆን፦ልብ ማለት ያለብን ግን እንዲህ ዓይነቶቹ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች በመላው አረብ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ከሶስተኛው ዓለም በመጡ ረዳትም ሆነ ደጋፊ የሌላቸው የጉልበት/የቤት ሰራተኞች ላይ የሚፈጸም የእለት ተእለት ተራ ድርጊት እየሆነ ከመጣ ዓመታት ተቆጥረዋል። ለዚህም እንደዋና ምክንያት የሚጠቀሰው ከፈላ የተባለውና በሳውዲ መንግስት ተዘጋጅቶ በመካከለኛው ምስራቅ በሚገኙ አገራት በስፋት እየተሰራበት ያለው
ከደሃ አገሮች ኑሯቸውን ለማሻሻልና ራሳቸውን ለመለወጥ በሚመጡ ወደ 25 ሚሊዮን የሚጠጉ ግለሰቦችን ስውር በሆነ መንገድ ለዘመናዊ ባርነት የዳረገ ዘረኛ እና በዝባዥ የአሰሪና ሰራተኛ  ውል/ስርዐት  ሲሆን አሰሪው ወይም ቀጣሪ ድርጅቱ በሰራተኞቹ ህይወት እንዳሻቸው ለመወሰን፡ለመቆጣጠር፡ለመሸጥ፡ለመለወጥ፡ለማሳሰር፡ለማሰቃየት፡ብሎም ለመግደል መንገድ የሚከፍት ነው። ስለዚህ መሰሪ ውል ብዙዎቻችን የምናውቅ አይመስለኝም፦ ስለዚህ ውል/ስርዐት በተለይም ኢትዮጵያውያን እህቶቻችን በግልጽ የሚያውቁት ወይም የተረዱት አይመስለኝም:: አብዛኛዎቹ ጉዞዋቸውን ወደ አረቡ ዐለም የሚያቀኑት ስለዚህ ከፈላ ውል/ስርአት አገናኝ ደላሎቹም ሆነ አሰሪዎቻቸው ዝርዝር መረጃ ሳይሰጧቸው በጣም ጥሩ ደሞዝ እንደሚከፈላቸው እና የተሻለ ኑሮ እንደሚኖሩ በመታለል ነው:: በከፈላ ስርዐት ምክንያት ዜጎቻችን ባልጠበቁት መንገድ የባርነት ወጥመድ ውስጥ እንዲገቡ ተደርገው; መብታቸው ተገፎ ለረሀብ:ለስቃይ:ለበሽታ:ለሞት:የአካል መጉደልና የአእምሮ ህምተኝነት:እስራት:አስገድዶ መደፈር: ሴተኛአዳሪነት ወዘተ እንዲጋለጡ የሚያደርግ ነው:: ይሄ ስርዐት አገናኝ ደላሎቹም ሆነ አሰሪዎቻቸው በወገኖቻችን ህይወት ላይ እንደፈለጉት ለማዘዝ መብት ስለሚፈቅድላቸው ከእነዚህ ወንጀሎች አንዱ ወይም አብዛኛው ቢፈጸሙባቸው እንኳን ወደ እነዚህ አገራት ለመጓዝ የተበደሩትን እዳቸውን ሳይከፍሉ ወደ አገርቤት እንዳይመልሷቸው በመፍራት  ለህግ አካላት ሪፖርት አያደርጉም ቢያደርጉም ተሰሚነት ያላቸው ተጠቂዎቹ ሳይሆኑ ወንጀለኞቹ ናቸው:: ለዚህም ነው ስለጉዳዩ በዝርዝር ማውራት የፈለግኩት። እስኪ ውሉ ምን እንደሚመስል በዝርዝር እንመልከት፦  ከፈላ  መሰረቱን ያደረገው የቢድዊን ጎሳ ዓባላት እንግዳ ተቀባይነትን ባህል ሲሆን በመጀመሪያ በስራ ላይ እንዲውል የተደረገው እ᎐አ᎐አ በ1950ዎቹ ሲሆን ዛሬ ግን ከዚህ ጥሩ ባህል ተቃራኒ በሆነ መልኩ ለአሰሪው/ቀጣሪ ድርጅት ባለቤት ከፍተኛውን ስልጣን የሚሰጥ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ናቸው
1ኛ አሰሪው/ቀጣሪው በስፖንሰርሽፕ መልክ ለሚመጡ ሰራተኞች የመግቢያ/መውጫ ቪዛ የማሰጠት፡ የህክምና፡የማህበራዊ፡ የህግ፡ የጤና እና ሌሎች አገልግሎቶች እንዲያገኙ/እንዳያገኙ የመፍቀድ/የማስፈቀድ ስልጣን ተሰጥቶታል።
2ኛ እነዚህ ሰራተኞች ተቀጥረው ሊሰሩ ተዋውለው በሄዱባቸው አገሮች እግራቸው ከረገጠ ጀምሮ የስፖንሰሩ/ኤጀንቱ/አሰሪው የግል ንብረት ይሆናሉ። ፓስፖርታቸውና ሌሎች የመጓጓዣ ሰነዶቻቸውን እንዲያስረክቡ በማደረግ ስፖንሰሩ/ኤጀንቱ/አሰሪው ሰራተኞቹን እንደፈለገው ለማሰራት፡ለማዋስ፡ለመሸጥ፡ እና የሚሰሩትን የስራ ዓይነት፡ ሰዓት መጠን፡እረፍት ወዘተ የሚወስን ሲሆን ሰራተኞቹ እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ የመቃወም ሆነ የመወሰን ምንም ዓይነት መብት የላቸውም።
3ኛ እነዚህ ሰራተኞች በህጋዊም ሆነ በህገወጥ መንገድ የሚገቡት ለሁለት ዓመት በሚቆይ የስራ ፍቃድ ቪዛ ሲሆን ስፖንሰሩ/ኤጀንቱ/አሰሪው ካልፈቀደላቸው ይሄ ሁለት ዓመት እስከሚያልቅ (አብዛኛውን ጊዜ ለዘላለም) ቢስማማቸውም ባይስማማቸውም ቀጣሪያቸውንም ሆነ የሚኖሩበትን/የሚሰሩበትን ቦታ ለመቀየር ምንም መብት የላቸውም።በዚህም የተነሳ በተቀጠሩበት ቤት እስረኛ ሆነው የሚኖሩ ሰራተኞች በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ናቸው።
4ኛ ስፖንሰሩ/ኤጀንቱ/አሰሪው ለሰራተኞቹ የሚያስፈልጉ እንደ መጠለያ፡ምግብ፡ህክምና የመሳሰሉት ጉዳዮች ሃላፊነት የተሰጠው ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ሰራተኞቹ የሚኖሩት በአሰሪዎቻቸው ቤት ወይም ቅጥር ግቢ ሲሆን፦እንደልባቸው የፈለጉበት ቦታ ለመዘዋወርና ለመንቀሳቀስ ያላቸውን ሰብዓዊ መብት በሚያግድ መልኩ እንዲኖሩ የሚያስገድድ ነው። እነዚህ መሰረታዊ ፍላጎቶች በስፖንሰሩ/ኤጀንቱ/አሰሪው በጎ ፍቃድ ላይ የተመሰረቱ ከመሆናቸውም ባሻገር ሰራተኛው እነዚህ ፍላጎቶች ሳይሟሉለት ቀርተው ስራውን ለመልቀቅ እንዳይችል የሚያግድ ስርዓት ነው። 
እነዚህ ከላይ የዘረዘርኳቸው የከፈላን ስርዓት መሰረት በማድረግ በመካከለኛው ምስራቅ በሚኖሩ ስፖንሰሮች/ኤጀንቶች/አሰሪዎች በጉልበት ሰራተኞች ላይ ከሚፈጸሙት የመብት ጥሰቶች ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ሲሆኑ እስኪ በምን ዓይነት መልኩ እነዚህ ወገኖቻችን ክብራቸው ተገፎ፡አካላቸው ተዋርዶ እና መብታቸው ተረግጦ ለረሃብ፡ለስቃይ፡ለእርዛት፡ለድብደባ፡ብዝበዛ፡አስገድዶ መደፈር፡ባርነት፡እስር ብሎም የዓእምሮ ህመምተኛ እንዲሆኑ እንደሚደረግ እንመልከት።
ለምሳሌ ዓለም ደቻሳን እንውሰድ፡ የሁለት ልጆች እናት በጣም በዝቅተኛ ኑሮ የምትኖር ሲሆን ድሃ ብትሆንም እጅግ ሳቂታ እና ተጫዋች እንደነበረች ወላጆቿና የሚያውቋት ተናግረዋል። ወደ ሊባኖስ የመጣችው በሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ተበድራ በህገወጥ መንገድ በሱዳን አቆራርጣ ሲሆን ዓላማዋ የቤተሰቧንና የራሷን ህይወት ለመለወጥ በሚል ነው። ሊባኖስ እንደገባች ስፖንሰር በማድረግ ቪዛ እንድታገኝ ያደረጋት ስፖንሰር/ኤጀንት/አሰሪ ንብረት ነበረች። እንደመጣች የሆነ ቤት ተቀጠረች እንግዲህ አስቡት ምግብ ተከልክላ፡ወይም የተበላሸ ምግብ ተሰጥቷት፡ተደብደባ፡ በአሰሪው ወይም/እና ወንድ ልጆቹ/ዘመዶቹ/ ተደፍራ፡ተሰድባ፡ተተፍቶባት፡ከዓቅሟ በላይ ስራ እንድተሰራ ወይም ለዘመድ/ለጓደኛ በውሰት ተሰጥታ አንዱ ወይም ሁሉም ተፈጽሞባት ሊሆን ይችላል እናም መስራት አልችልም ስላለች ስፖንሰሯ/ኤጀንቷ/አሰሪዋ ከሌላ አሰሪ አገናኝቷት እዛም ተመሳሳይ ችግር/ሮች አጋጥሟት መስራት አልቻለችም/አልፈለገችም። እናም ስፖንሰሯ/ኤጀንቷ/አሰሪዋ እንዳየነው አገሯ ኤምበሲ ፊትለፊት ጸጉሯን ጨምድዶ መንገድ ለመንገድ እያላጋ መኪናው ከተታት በኋላ በመጨረሻ የአእምሮ ሆስፒታል ውስጥ ራሷን አጠፋች ተባለ። አስቡት እቺ ልጅ ብታብድ ያንሳታል፦የተበደረችው ገንዘብ ለመክፈል አለመቻል፡በአሰሪዎቿ የደረሰባት ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ተጨማምሮ እንኳን ማበድ ለሌላም ያደርሳል። እ.ኤ.አ በ 2008  ሂዩመን ራይትስ ዎች ሊባኖስ ውስጥ ከሌሎች ሀገራት የመጡ የቤት ሠራተኞችን ሞት አስመልክቶ መረጃዎችን አጠናቅሮ ነበር። በዚህም መሠረት ራስን ማጥፋትንና ከረጅም ሕንጻዎች ላይ መውደቅን ጨምሮ ተፈጥሮአዊ ባልሆኑ ምክንያቶች በአማካይ በሳምንት አንድ ሞት ተመዝግቦአል። በመላው ዓለም ካሉ መንግስታት እጅግ ለዜጎቹ ክብርና ደህንነት በመቆርቆር የማይታማው ልማታዊ መንግስታችንም 45ሺህ እህቶቻችንን/ልጆቻችንን ወደ ሳውዲ ለመላክ ስምምነቱን በመፈረም የከፈላ ስርዓቱ ተቋዳሽ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቋል፦ምንም እንኳን በመካከለኛው ምስራቅ አገራት የሚገኙ የተከበሩ እና የተወደዱ ዲፕሎማቶቻችን ኤምበሲዎቻችን ወደ አስከሬን ማቆያነት እየተጠቀሙባቸው ከገለጹ ሰንበትበት ቢሉም። እንዴ ብድር በምድር አይደል የሚባለው እኛ ልጅ እግሩ ፕሬዝዳንታችን (እድሜያቸውን የማስቱላ ያድርግልንና) እንዲህ ሲያስነጥሳቸውም/ጉንፋን ሲዛቸውም ሳውዲን የውሃ መንገድ ያደረጉት ያለነገር ነው ትላላችሁ። እነ ፍሊፒንስና ኢንዶኔዢያ መንግስታት ከዚሁ ሁሉ ውርደት እና ስቃይ የፔትሮ ገንዘብ ይቅርብን ብለው ዜጎቻቸውን ለስራ (ባርነት ብለው ይቀላልወደ ሳውዲ አረቢያ የሚልኩ ቀጣሪ ድርጅቶችን ማገዳቸው ልብ ይባልልኝ። ስለ  ከፈላ  ስርዓት የማያውቅ እና የኢትዮጵያውያን ሴቶችን ባርነት በመካከላኛው ምስራቅ ያላየ በርካታ የዓለም ህብረተሰብ ባርነት ከዚህ ምድር ላይ ከ200 ዓመት በፊት እንደተወገደ ቢነግራችሁ አትገረሙ። ሳውዲዎች የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ ነው ነገሩ፦ከ 400 ዓመት በፊት ከአፍሪካ ባሪያ በመፈንገል የሰራችሁት በደል እንዳይበቃ ዛሬም በከፈላ  ስም ዜጎችን ለዘመናዊ ባርነት፡ብዝበዛ፡እስራት፡አስገድዶ መድፈር፡ እና ወዘተ ሌሎች እጅግ ዘግናኝ ኢሰብዓዊ ወንጀሎች መዳረግ ነገ በታሪክ ፊት ተጠያቂ እንደምትሆኑ ልታውቁ ይገባል። ከማብቃቴ በፊት፡ለልማታዊ መንግስታችን አንድ ጥያቄ አለኝ፦ እንዲህ ኖርዌይ በሰላም፡በነጻነት እና ተከብረው የሚኖሩትን ኢትዮጵያውንን ለማስመለስ ደፋ ቀና ስትሉ ምነው እነዚህ በአረብ ዓገራት እንደ ቁም ከብት በገመድ ታስረው ቀን ከሌሊት ያለማንም አስታዋሽ ፍዳቸውን የሚበሉና በየማጎሪያው ስለሚገኙ በሺህ የሚቆጠሩ እህቶቻችን ከእነዛ አስክሬን ገናዥ ዲፕሎማቶቻችሁ አልሰማችሁም ወይም አላያችሁም ማለት ያስቸግራል:: መቼም ኖርዌይም ያሉትም አረብ አገር ያሉት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው፦ ህምም ነገር ኧለዎ አለ ጫላ  

No comments:

Post a Comment