Thursday, May 31, 2012

ለታደሰ ሙሉነህና የእሁድ ጠዋት ፕሮግራም መታሰቢያ

ኧቤት የዚህን ተወዳጅ ፕሮግራም መግቢያ ሙዚቃና የታደሰ ሙሉነህ ማራኪ ድምጽ በስንት ዘመኔ ስሰማው የተሰማኝ የደስታና የሃዘን ቅልቅል ነው፦( ታደሰ ነፍስህ በሰላም ትረፍ።  በኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ሌሎች ሚዲያዎች ከ40 ዓመታት በላይ ያገለገለው ጋዜጠኛ ታደሰ ሙሉነህ ቀብር ባለፈው ዓርብ ግንቦት 16 2004 ዓ᎐ም᎐ በገነተ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡ የ 64 ዓመቱ ጋዜጠኛ ታደሰ ሙሉነህ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ከዜና አንባቢነት እስከ ዜና ዋና አዘጋጅነትና በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ከማገልገሉም በላይ፣ ከ1970ዎቹ መጀመርያ ጀምሮ ተወዳጅ የነበረው ‹‹የእሑድ ጧት ፕሮግራም›› መሥራችና ዋና አዘጋጅ ነበረ፡፡ 
አቶ ታደሰ ጡረታ ከወጣም በኋላ ከሙያው ሳይለይ የራሱን ማስታወቂያ ድርጅት በማቋቋም የማስታወቂያ ሥራዎችን ከማከናወኑ ባሻገር፣ በሸገር ኤፍኤም የ‹‹እሑድ እንደገና›› ፕሮግራም አዘጋጅና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የራዲዮ ፕሮግራም ይመራ ነበር፡፡ በሙያው ካገኛቸው በርካታ ሽልማቶች መካከል ከኢትዮጵያ የሥነ ጥበባትና መገናኛ ብዙኀን ሽልማት ድርጅት ያገኘው በዋናነት ይጠቀሳል፡፡
ታደሰ ሙሉነህ እና ባልደረቦቹ (ባልሳሳት የአሜሪካን ድምጽ አማርኛ ክፍል ባልደረባ አዲሱ አበበ አንዱ ነበር)  በኢትዮጵያ የመዝናኛ ሬዲዮ ፕሮግራም ዘርፍ
ፈርጅ ቀዳጆች ቢባሉ አያንሳቸውም። በዛ የደርግ የጨለማ ዘመን እንጨት እንጨት የሚል ፕሮፓጋንዳ በየእለቱ በምንጋትበትና እንደዛሬው ኢንተርኔት ዲቪዲ/ቪድዮ፡ ቪድዮ ጌም፡ ሞባይል፡ፌስቡክ፡ዩ ትዩብ፡ የ24 ሰዓት ኤፍ ኤም ሬዲዮ ሳተላይት ዲሽ ባልነበረበት ወቅት ዋነኛ መዝናኛችን የእሁድ ጠዋት ፕሮግራም ነበር። ኧቤት ያቺ ከርካሳ ፕሊፕስ ሬዲዮ ውለታዋ መቼም አይረሳ። አንዳንዴ እሷም ትበላሽና ጎረቤት ሄደን የምናዳምጥበት ጊዜ ነበር። ዛሬማ እድሜ ለቴክኖሎጂ ሬዲዮ ባይኖርህ፡በኢንተርኔት አለዚያም በሞባይል ታዳምጣለህ፡ ፕሮግራም ቢያመልጥህ ኢንተርኔት አርካይቭ አለልህ። አንዳንዴ ሳስበው ስንት ፐርሰንቱ የዚህ ዘመን ትውልድ  ሬዲዪ የሚባለውን ነገር በአካል አይቶት ይሆን የሚል ጥያቄ ይጭርብኛል። እንደው ሬዲዮስ ስራዬ ብሎ እሚገዛ ሰው ይኖር ይሆን፡  አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ሬድዮ ምን ያህል ደረጃ እንዳለው አላውቅም፡ነገርግን እዚህ ባለሁበት አገር የሬዲዮ ስሙን እንጂ ምን እንደሚመስል እንኳን የማያውቁ ልጆች እንዳሉ ለመገመት አያዳግትም።   

ለእኛ ዘመን ትውልድ እሁድ ልዩ ስፍራ ነበራት እድሜ ለታደሰ ሙሉነህ እና ባልደረቦቹ። እሁድ ደርሳ የጠዋት መዝናኛ ፕሮግራም ለመስማት የነበረን ጉጉት ዛሬም ድረስ ሳታውሰው ግርም ይለኛል። በዚህ ላይ ፕሮግራሙን በየሳምንቱ ለመከታተል ከነበረን ጉጉት የተነሳ ቤት ውስጥ የምንታዘዘውን ስራ በቅድሚያ አጠናቀን ነበር የምንጠብቀው።ሰፈራችን ከእያንዳንዱ ቤት በሚወጣው የእሁድ ጠዋት የሬዲዮ ፕሮግራም ድምጽ ድምቅ ትል ነበር። ትዝ ይላችኋል ምንታዝበዋል፡እርሶም ይሞክሩት፡ሳምንታዊ ትረካዎች፡ተከታታይ ድራማዎች፡ አጉል ጸባይ እና የመሳሰሉት ዝግጅቶች? እንዴት ለዛ ነበራቸው! ፕሮግራሙ ሲያልቅ ደሞ የነበረ ድብርት አይነሳ። በዚህ አዲስ ትውልድ  እድለኛነት በአንድ በኩል ስቀና በሌላ በኩል አዝናለሁ። መቼም እንደኛ ዘመን ቤተሰብ ተሰብስቦ ሬዲዮ ማዳመጥ በአሁን ዘመን እየቀረ የመጣ ልምድ ይመስለኛል ተሳስቼ ካልሆነ፡ ይሄ የሚያሳየው ምን ያህል ቴክኖሎጂ በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን  ከማቀራረብ ይልቅ እያራራቀ እንደሆነ ሳስብ ምን ዓይነት ትውልድ ወደፊት ሊፈጠር እንደሚችል መገመት እራሱ ያስፈራል። ለማንኛውም የታደሰ ሙሉነህና የመላው እሁድ ጠዋት ፕሮግራም አዘጋጆች ውለታ እንደኔ ላለው "የጠፋው ትውልድ" ያበረከተው ውለታ መቼም አይዘነጋም።   

No comments:

Post a Comment