Wednesday, October 31, 2012

የተረሱት የመንግስት ጋዜጠኞችሌሊሴ ወዳጆ የህሊና አስረኛ  
አገራችን ከቅርብ አመታት ወዲህ እድሜ አሁን በህይወት ለሌሉት ባለራዕዩ ልማታዊ መሪያችን እና ፓርቲያቸው፡ በተለያዩ ምክንያቶች ታዋቂነቷ እየገነነ መጥቷል።ሌላ ሌላውን ትትተን በፈረንጆቹ የ2012 ዓመት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ጋዜጠኞችን በማሰር ሁለተኛነትን ስተቀዳጅ፡አንደኝነቱን ግን ጎረቤታችን ኤሪትርያ ነጥቃናለች፡ወይ ነዶ፡እንዴት ተድርጎ። ምስጋና ለታላቁ መሪያችን ነፍሳቸውን ይማረውና (ይቅርታ ተዳፈርኩ አይደል፡ለካ አልሞቱም የሚሉ አንዳንድ ወገኖች እንዳሉ ዘንግቼው ነው)፡ አገራችን ባለፉት አስርተ ዓመታት ጋዜጠኞቿ እንዲሰደዱ በማድረግ በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠቀሱት አገሮች ተርታ ውስጥ ትገኛለች። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞቿ በማሸለም ታዋቂ ሆናለች። የሩቁን ትተን በዚህ ዓመት ብቻ ሁለት በሽብርተኝነት እና አገር በመካድ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው ቃሊቲ በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞቿ ማለትም እስክንድር ነጋ እና ርዕዮት ዓለሙ ከሁለት የተለያዩ የዓለም ዓቀፍ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ተሸላሚ ሆነዋል። አብዛኛውን ጊዜ የመገናኛ ብዝሃንም ሆነ በመብት ተሟጋች ድርጅቶች በግሉ የሚዲያ ዘርፍ የሚያገለግሉ ጋዜጠኞች ሲታሰሩ በብዛት የሚያሰሙት ድምጽ
በመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ተቀጥረው የሚሰሩ ጋዜጠኞች ሲታሰሩ ጎልቶ ለምን እንደማይሰማ ሁልጊዜም የሚከነክነኝ ነገር፡ ነው። እስቲ ስንቶቻችን ሌሊሴ ወዳጆሺፈራው ኤንሰርሙዳበሳ ዋቅጂራሃይለየሱስ ወርቁአብዱልሰመድ መሃመድ እና የመሳሰሉትን ስሞች ከዚህ በፊት ሰምተናል? በርግጠኝነት የአብዛኛዎቹን ስም ጭራሽ ሰምተነው አናውቅም ወይም እንግዳ ናቸው።

የመብት ተሟጋቾች ድርጅቶች ዝምታ፣ግን ለምን???

በኔ ግምት ይሄ ችግር ሊመነጭ የቻለው አብዛኛው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ፡የመገናኛ ብዙሃንና አንዳንድ የመብት ተሟጋቾች ድርጅቶች በመንግስት መገናኛ ውስጥ ተቀጥረው ለሚያገለግሉ ጋዜጠኞች ባለው የተሳሳተ አመለካከት የተነሳ እነዚህ ጋዜጠኞች የመንግስትን ፕሮፓጋንዳ ከማስተጋባት ካለፈ ውጭ የመንግስትን ፓሊሲዎች በመተቸታቸው ወይም በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት ሊታሰሩ፡ከስራ ሊባረሩ ወይም ሌሎች የሰብዓዊ ጥሰቶች ሊደርስባችው እንድማይችል አድርጎ ከማሰብ የመነጨ ይመስለኛል። አንዳቸውም እነዚህ የመብት ተሟጋቾች ድርጅቶች በቅርብ ዓመታት ባወጡዋቸውና በኢትዮጵያ ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙ የጋዜጠኞች ወይም የህሊና እስረኞች ስም ዝርዝር ውስጥ  በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በኦሮምኛው ክፍል ሲያገለግሉ በነበሩበት ጊዜያት ለኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ መረጃ ታቀብላላችሁ ተብለው የታሰሩትን ሌሊሴ ወዳጆና ሺፈራው ኤንሰርሙ የተባሉት ተጠቂዎችን አልገለጹም። እነዚህ ከላይ የጠቃቀስኳቸው ግለሰቦች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥና ሬድዮ ድርጅት ተቀጥረው በሚያገለግሉበት ወቅቶች በተለያዩ ጊዚያት ለእስር የተዳረጉ፡በእስር ላይ የሚገኙና አንዳንዶቹም ደብዛቸው የት እንዳለ የማይታወቅ ናችው። እስኪ በሌሊሴ እንጀምር

የሶስት ልጆች እናት እስርቤት አባት በስደት

ይህች የሶስት ልጆች እናት የሆነችውና በኢትዮጵያ አቆጣጠር ህዳር 2001 ከ ኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ ጋር ግንኙነት አለሽ ተብላ ተወንጅላ ከዛም በዚሁ በተከሰሰችበት ወንጀል ጥፋተኛ ነሽ ተብላ በሚያዚያ ወር 2003 ዓም ፍርድቤቱ ባሰተላለፈው ውሳኔ መሰረት 10ዓመት ያለይግባኝ የተፈርደባት ሲሆን፡ በቅርቡ ለፍ/ቤቱ ያቀረበችው የይግባኝ ማመልከቻ ውድቅ እንደተደረገ ሃይለየሱ ወርቁ የተባለውና ከአብዱልሰመድ መሃመድ ጋር በሙሰኝነት ክስ ተመስርቶበት አሁን በስደት ከኢትዮጵያ ውጭ በመኖር ላይ የሚገኘው የቀደሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ባልደረባ ገልጾልኛል። እጅግ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ የሌሊሴ ባለቤት የነበረው ዳበሳ ዋቅጂራ ከሷ ቀደም ብሎ በተመሳሳይ ወንጀል ተከሶ በ1996 ታስሮ ከዛም በ2001 ከእስር ሲለቀቅ አገር ጥሎ በመጥፋቱ፡በአሁን ሰዓት ሶስት ጨቅላ ልጆቻቸው ያላሳዳጊ ተበትነው ይገኛሉ። ታዲያ ለእነ እስክንድር፡ለእነርዕዮት፡ለእነውብሸት ስንጮህ፡ሌሊሴን እና ልጆቿን እንደሌሉና እንዳልተፈጠሩ መዘንጋት ከማዳላት ውጭ ምን ሊባል ይችላል።

ሽፈራው ኤንሰርሙን ያያችሁ !!!

ሌላው የኢቲቪ የቀድሞ ባልደረባዬ እና ከሌሊሴ ባለቤት ጋር በ1996 ከታሰረ በኋላ በተደጋጋሚ ሲፈታና ሲታሰር ቆይቶ እንደገና በጥር ወር 1997 ዓም ከታሰረ በኋላ በአሁን ወቅት ዱካው ጠፍቶ ይገኛል። አንዳንድ ጋዜጦች ሽፈራውና ዳበሳ አብረው በእስር በነበሩባቸው ጊዚያት በእስርቤት ባለስልጣናት ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸማባቸውና ለደረሰባቸው አካላዊ ጉዳትም ምንም ህክምና እንዳልተደረገላቸው ዘግበዋል። ሽፈራው ከእስር ተለቆ በነበረበት ጊዚያት ወደ ስራ ገበታው እንዲመለስ ያቀረበው ጥያቄ በቀጣሪው መ/ቤት ተቀባይነት አለማግኘቱም ይታወቃል። ደብዛውን ለማግኘት በጉግል ደረገጽ ባደረግኩት ማፈላለግ፡ያገኘሁት መረጃ በጣም የቆየ እና አሁን የት እንዳለ የማይጠቅስ ሲሆን፡ለ 14ወራት ያህል ታስረው በኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ መባቻ ላይ ከቃሊቲ እስርቤት የተፈቱን ሁለቱን ስዊድናዊ ጋዜጠኞች በቅርቡ ስለ ሽፈራው ደብዛ የሰሙት ነገር እንዳለ ጠይቄያቸው ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ነግረውኛል። ሽልማቱና ሙገሳው ቢቀር ለሌሎች በግሉ ዘርፍ ሲሰሩ ለነበሩና አሁን በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ የምናደርገው ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ ሌሎች መሰል ዝግጅቶች እንደምን ለእነ ሌሊሴ ወዳጆና ሽፈራው ኤንሰርሙ ተነፈገ? በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እንደሆነ እሱ ከሚፈቅደውና ከሚያራምደው የፖለቲካ አመለካከት የሚቃረኑ የሚመስሉትን በስሩ ሲያገለግሉ የነበሩትንም ሆነ የግሉ ዘርፍ ጋዜጠኞችን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፡ደጋፊዎች፡አባላት እንዲሁም ማንኛውንም ተራ ዜጋ ከማዋከብ፡ከማሰር እና ከመግደል ወደኋላ ያለበት ጊዜ የለም። እናም ልዩነት ሳናደርግ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የሚፈጽማቸውን የሰብዓዊም ሆን የግለሰብ መብት ጥሰቶች በማጋለጥ በህገወጥ መንገድ ባልሰሩት ወንጀል በአገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ እስር ቤቶች በከፍተኛ ስቃይና እንግልት ላይ የሚገኙ በሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ባስቸኳይ እና ያለምንም ቅድመሁኔታ እንዲፈቱ በየጊዜው መወትወት ዋናው የወቅቱ ተቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን ይገባል። 

No comments:

Post a Comment