Tuesday, July 17, 2012

አዎ መለስ ዜናዊን ያቆይልንኧረ እስቲ አትቸኩሉ ስም ለመስጠት። መቼም የዛሬውን የጦማሬን ርዕስ ገና ስታዪት፡ ምን እንደምትሉ ልገምት?አበደ፡ለየለት፡ ወይም ወያኔ ሆነ እናም ሌሎች 101መላምቶች ሊሆኑ ይችላሉ። የዛሬውን ጦማር እንድጦምር ያነሳሰኝ ግን ጉዳዩ ወዲህ ነው። ትናንት ወደ ምሽት አካባቢ እቺን ብቅ ጥልቅ እያለች ያስቸገረች ጸሃይ ሳታመልጥ ለመሞቅ እዚህ ስቶክሆልም በብዛት ሰው ወደሚሰበስብሰብት አካባቢ ስሄድ አንድ በቅርቡ የተዋወቅኳትን ኢትዮጵያዊ መንገድ ላይ አገኘኋት። ከላይ እጅጌው ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማ ቀለማት ያሉበት ጃኬትና፡ከታች ደግሞ ጥቁር ጥብቅ ያለ ሱሪ እና ሳንዳል ጫማ ተጫምታለች።ሰላም ከተባባልን በኋላ እንኳን ደስ አለህ አለችኝ ፊቷ በደማቅ ፈገግታ ተሞልቶ፡እኔም ልቤ በደስታ ጮቤ እየረገጠ ለምኑ አልኳት? በመቀጠልም እንዴ አልሰማህም ዛሬ ጠዋት መለስ ዜናዊ መሞቱን።በአንድ ጊዜ ደስታዬ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ቸለሰችበት። ልብ በሉ ከእሷ ጋር ከመገናኘቴ ጥቂት ደቂቃዎች በፊት ኢንተርኔት ላይ ዜናዎችን ሳነብ ስለተከበሩትና ተወዳጁ ጠቅላይ ምኒስትራችን መሞት አንዳችም የተጠቀሰ ነገር የለም፡ታመው ቤልጂየም በህክምና ላይ እንደሚገኙ ከመጠቀሱ በስተቀር። እናም ይሄንኑ ነግሪያት ያበሰረችኝ "ብስራት" ትክክል እንዳልሆነ ላሳምናት ብሞክርም ሌሎች አዲስ እና ነባር ኢትዮጵያዊ ተቃዋሚ ቡድኖች ያወጡዋቸውን መግለጫዎች በመዘርዘር ልታሳምነኝ ሞከረች። 
እንደውም በኋላ እንደተረዳሁት  ቦርሷዋ ውስጥ በቁጥር ጥቂት የማይባሉ 
የኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማዎች በመያዝ ከምትኖርበት አካባቢ ወደ 1ሰዓት ተኩል ተኩል አካባቢ መንገድ ተጉዛ የመጣችው ይህንን የምስራች በደስታ በሆታና በእልልታ መሃል ከተማ በሚገኘው የሰርጌልስ አደባባይ ከሌሎች መሰሎቿ ጋር ለማክበር ነበር። ነገርግን እንዳሰበችው ሳይሆን አመሻሽ ላይ ወደቤቷ ተመለሰች።በርግጥም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የዚህቺን የዋህ ኢትዮጵያዊ ሃሳብ የሚጋሩ ወገኖች በመላው ዓለም እንደሚገኙ በተለያዩ ድረገጾች የውይይት መድረኮች በፌስቡክ እና በአንዳንድ በውጭው ዓለም በሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን ላይ ከሚሰጡ ስሜታዊ እጅግ በሳል ካልሆኑ አስተያየቶች ለመረዳት አዳጋች አይደለም። ባጭሩ አዎ እኔ መለስ ዜናዊ ከህመማቸው በደንብ እንዲፈወሱ ከሚመመኙት ወገኖች አንዱ ነኝ፡ዛሬ ድንገት ወድጄያቸው፡ ወይም አንዳንድ ወገኖች እንደሚያስቡት ወያኔ ሆኜ ሳይሆን ሚከተሉት ምክንያቶች ነው። አቶ መለስ እንደማንኛችንም ስጋ ለባሾች ሟች ሲሆኑ በአሁኗ ደቂቃና ሰከንድም ሞተውም  ሊሆን ይችላል ወይም ነገ፡ከነገወዲያ፡የዛሬ ዓመት የዛሬ 50ዓመትም ሊሞቱ ይችላሉ። ዋናው ጥያቄ ግን አቶ መለስ ዛሬ ቢሞቱ እንደዛች የዋህ እና ስሜታዊ የሆኑ ወገኖች ከሳቸው ሞት ምን ሊጠቀሙ ወይም ሊያተርፉ እንደሚችሉ ሳስብ ግርም ይለኛል። በመለስ ድንገተኛ ሞት ከማንም በላይ የሚጎዳው ለሃያአንድ ዓመታት በእስር፡በረሃብ፡በጦርነት፡በበሽታ፡በሙስና፡በመልካም አስተዳደር እና የህግ የበላይነት እጦት እና የመሳሰሉት ችግሮች ከአዲግራት እስከ ሽላቦ፡ከመተማ እስከ አፋር፡ከአሶሳ እስከ ኦጋዴን፡ከጋምቤላ እስከ ደምቢዶሎ፡ከአዲስአበባ እስከ ወልቂጤ ሲቀጣ የኖረው በሚሊዮን የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ እንጂ መለስማ አንዴ ከሞቱ፡ሞቱ ነው። እንደውም ለእሳቸው ግልግል ነው በነዚህ ሁለት ዓስር ዓመታት ለፈጸሟቸው ግፎች፡ለገደሏቸው ንጹሃን ዜጎች፡በእስር፡በረሃብና፡በጥማት ላሰቃዩዋቸው እና ከአገር እንዲሰደዱ ላደረጉዋቸው ወገኖች በአለም ዓቀፉ ፍርድቤት እንደ የላይቤሪያው የቀድሞ መሪ ቻርልስ ቴይለር  የግብጹ አምባገነን ሆስኒ ሙባረክ፡ እንደ ቱኒዚያው ዘይን ቤን አሊ፡ እንደዩጎዝላቪያዊው ሰውበላ ስሎቦዳን ሚሎሶቪች እና ሌሎችም ወንጀለኛ አምባገነኖች በፍርድ ሳይጠየቁና በሰፈሩት ቁና ሳይሰፈሩ ቢሞቱ ነው የማዝነው። እነ እስክንድር ነጋርዕዮት ዓለሙአንዷለም አራጌኦልባና ሌሊሳ በቀለ ገርባፕሮፌሰር አስራት ወልደየስብርቱካን ሚደቅሳማርቲን ሺቢዬዮሃን ፐርሹን እና ሌሎችም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ባለሰሩት ወንጀል በእስር ላይ የሚማቁ ወገኖቻችን ነጻ ተለቀው የእነሱ አሳሪዎች በተራቸው ማለትም አቶ መለስና ጭፍራዎችቸው በቃሊቲማእከላዊሸዋ ሮቢትዴዴሳ እና በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በሚገኙ እጅግ አስከፊና ዘግናኝ እስርቤቶች ለዓመታት መታሰር ምን እንደሚመስል እንዲያዩት ወገኖቼ አሁንም ደግሜ እላለሁ፡መለስ ዜናዊን ያቆይልን እድሜያቸውን አርዝሞ እነሱ ተከሳሽ እኛ ከሳሽ የምንሆንበት እና በስደት በመላው ዓለም እንደ ጨው ዘር ተበትነን የምንኖር ወገኖች አገራችን ገብተን በሰላም፡በነጻነት እና ያላንዳች ፍርሃትና መሸማቀቅ፡አንገታችንን ቀና አድርገን በራስ መተማመን ሃሳባችን በነጻ የምንገልጽበት እና የመረጥነውን የምንሾምበት፡ ያልፈለግነውን ደግሞ ከስልጣን የምናወርድበትን ስርዓት አቶ መለስ ሳያዩ ቢሞቱ የተጎዳነው እኛ እንጂ እሳቸውማ ከነወንጀላቸው ወደማይቀረው ዓለም ተሰናበቱ። እናም አቶ መለስ እድሜዎን የማቱሳላ መኖሪያዎን ደግሞ ቃሊቲ  ይሆን ዘንድ ልማታዊ ምኞቴን አቀርባለሁ። 
ከሰላምታ ጋር
ፊርማ የማይነበብ

No comments:

Post a Comment