Wednesday, November 19, 2014

እውቁ ገጣሚ፤ጽሃፊ፤ባለቅኔ፤ ገሞራው ከአርባ ዓመት ስደት በኋላ ዐረፈ

... እንደ ኪሩብ ሁሉ - ክንፍ አካል ቢኖረኝ፣
መች እጠበስ ነበር - በዚህ ዓለም በቃኝ፣
ስላጣሁ ብቻ ነው - መሸሻ መድረሻ
በዚች በሽት ዓለም - የኖርኩ እንደውሻ ...፣"
"... በሥጋዬ ብቻ ውጪ - ሀገር እስካለሁ፣
እወቁልኝ በርግጥ - አልኖርኩም ሞቻለሁ! ...
ኃይሉ (ገሞራው)

በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ታዋቂ የነበረው ደራሲ፣ ገጣሚና ባለቅኔ ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) እሁድ ጥቅምት 30 ቀን 2007 .. (ኖቨምበር 92014) በስደት በሚኖርባት ስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም በ71 ዓመቱ ከዚህ ዓለም ተለየ። ሥርዓተ ቀብሩ በስዊድን እንደሚፈፀም ታወቀ። 
ከጥንት ጀምሮ ስናየው የኖርነው፡
ሲነድ ሲቃጠል የሚስቅ እሳት ነው። 
ይህንን ስንኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበብኩት ስምንት ወይም ዘጠኝ ቢሆነኝ ነው። ኃይሉ ገሞራው  መጽሃፎች የቤታችን መጽሃፍት መደርደሪያ ካጣበቡት መካከል በቅድሚያ ይጠቀሳሉ።  የረከተ መርገም ረቂቅ እንደወረደ፡ በገሞራው ወይም በሌላ አርታኢ በቀይ ብርዕእርማቶች፡ ከገጽ እስከ ገጽ ተገጥጠውበት ነበር። የኃይሉ ገሞራው መጽሃፍት፡  አማርኛ ስነጽሁፍ ጋር አስተዋውቀኛል ብል ማጋነን አይሆንም። ከዘመናት በኋላ እዚህ፡ ስዊድን በስደት በ2004 ዓም የኢትዮጵያ  አዲስ ዓመት አከባበር ላይ ፡  ርቀት፡ ይህን እውቅ ደራሲ ለማየት ችያለሁ። እንዳለመታደል ሆኖ፡ተቀራርበን ለማውጋት አልቻልንም። ባለበት የጤንነት ችግር ምክንያት ዝግጅቱ ሳይፈጸም ወደ ቤቱ ሄደ፡ ከዛ በኋላም ለመገናኘት እድሉ አልተፈጠረም። የኛ ነገር በጅ የያዙት ወርቅ ሆነና እንጂ፡ የኃይሉ ገሞራውን ለትውልድ የሚተላለ፡ ወደር የሌለው ትምህርት እና እድሜ የጠገበ የስነጽሁፍ ክህሎት በተለያየ መንገድ ማቆየት በቻልን ነበር። ምን ዋጋ አለው፡ ጅብ ከሄደ ሆነ ነገሩ። ጋሽ ኃይሉ በምድር ለሰባት አስርት ዓመታት በቆየህባቸው ጊዚያት ደስታን የተነፈገችው ንጽሁ ነፍስህ በሰላም ትረፍ።(የጸሃፊው ማስታወሻ)
በአዲስ አበባ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አካባቢ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1935 .. ከእናቱ ከወ/ሮ አመለወርቅ ሀብተወልድ እና ከአባቱ ከመሪጌታ ገብረዮሐንስ ተሰማ የተወለደው ደራሲ፣ ገጣሚና ባለቅኔ ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) ትምህርቱን የጀመረው
በአባቱ በመሪጌታ ገብረዮሐንስ አማካኝነት በቤተክህነት ነበር። አራት ኪሎ በሚገኘው ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን በዲያቆንነት እያገለገለ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ካጠናቀቀ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (ከቀድሞው አፄ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ) በመግባት ከቋንቋዎች ጥናት ተቋም የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል።

ደራሲ፣ ገጣሚና ባለቅኔ ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) በአማርኛ፣ በግዕዝ፣ በእንግሊዝኛ እና በቻይንኛ ቋንቋዎች በመጻፍ ይታወቅ ነበር። በተለይም በአማርኛ ቋንቋ ያበረከታቸው ሥራዎቹ በኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ላይ የራሱን አሻራ እንዲያሰፍር ከማድረጋቸውም በላይ በዘመናዊው የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ የራሱ የሆነ ጉልሕ ድርሻ እንዲኖረው አስችለውታል።

ደራሲ፣ ገጣሚና ባለቅኔ ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) የታተሙ ከሰላሳ በላይ የሚሆኑ ሥራዎች ያሉት ሲሆን፣ ከመቶ የማያንሱ ለሕትመት ያልበቁ ወጥና ያለቁ ሥራዎች እንደነበሩት በሕይወት እያለ ቅርቡ የነበሩ ሰዎች ይናገራሉ። ከሚታወቅባቸው በርካታ ሥራዎቹ ውስጥ "በረከተ መርገም" የተሰኘው ግጥም በቀዳሚነት የሚጠቀስ እንደሆነ ይታወቃል። ሥራዎቹ ለበርካታ ወጣቶች ብርታትና ኃይል እንደሰጡ ብዙዎች ይመሰክሩለታል።

በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በሥራዎቹ ተቺነት የተነሳ ለእስር ተዳርጎ የነበረው ኃይሉ ገብረዮሐንስ፣ ከእስር ከተፈታ በኋላ በአዲስ አበባ የመምህራና ማሠልጠኛ ኮሌጅ ማስተማሩን ቀጥሎ ትንሽ እንደቆየ ለተልዕኮ ትምህርት (ስኮላር) ወደ ቻይና አቅንቷል። የቻይናን ሥነጽሑፍ ለማጥናት በቤጂንግ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እየተማረ ሳለ፣ በሦስት ዓመት ውስጥ ቻይንኛን አቀላጥፎ በመቻሉና በቻይናውያን ፍልስፍና ላይ ያለውን ድክመትና ጥንካሬ ላይ አብጠልጥሎ በማወቁ በዩኒቨርሲቲው ይማሩ በነበሩ ቻይናውያንና ከውጭ ሀገር በመጡ ተማሪዎች መሃከል ከፍተኛ ዝናን አትርፎ ነበር።

በቻይና ለሰባት አመታት የቆየ ሲሆን፣ ለዶክትሬት የመመረቂያ ጽሑፉ የመረጠው ርዕሰ ጉዳይ አናርኪዝም በቻይና ቋንቋ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ በተመለከተ ስለነበር፤ የቻይና ባለሥልጣናት በመንግሥታቸው ላይ የፖለቲካ ትችት ያስከትልብናል ብለው በማመናቸው ከሀገር እንዲወጣ አድርገውታል። በወቅቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ዩኔኤችሲአር አማካኝነት ኖርዌይ በጥገኝነት ተቀብላው ነበር። ከዚያም ወደ ስዊድን በማቅናት በስቶክሆልም ዩኒቨርሲቲ በሚገኘው የቻይና ቋንቋ ዲፓርትመንት በቻይና የጀመረውን ትምህርት ለመቀጠል ጥረት ያደረገ ሲሆን፣ ወደ ቻይና ሄዶ ለጥናቱ አስፈላጊ መረጃዎችን እንዲያሰባስብ በአማካሪው አማካኝነት የቻይናን ኤምባሲ ሲጠየቅለት ኤምባሲው ቪዛ ከልክሎታል።

የኖርዌይ መንግሥት ከሀገር ወጥተህ ከተወሰነ ጊዜ በላይ ቆይተሃል በሚል የመኖሪያና የሥራ ፈቃዱን ከልክሎት ስለነበር በስዊድን በድጋሚ ጥገኝነት ለመጠየቅ ተገድዷል።

ደራሲ፣ ገጣሚና ባለቅኔ ኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) ወደ አርባ ዓመት በስደት የኖረ ሲሆን፣ በርካታዎቹን የስደት ዓመታት በኖረባት በስዊድን የቀብር ሥነሥርዓቱ እንደሚፈፀም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ለዘመዶቹ፣ ለወዳጆቹ፣ ለአፍቃሪዎቹ፣ ለአድናቂዎቹና ለመላው ሥነጽሑፍ አፍቃሪያን መጽናናትን ትመኛለች።


No comments:

Post a Comment