Monday, December 31, 2012

የእናት ቤት ይሻላል ዘንጋዳ ደረቁ

ያሰኛል ይሄን ከዚህ በታች ያለውን የአንዲት በዴንማርክ አገር ለሚገኙ ግለሰቦች በጉዲፈቻነት ተስጥታ በወላጆቿ ናፍቆት የተነሳ በአሳዛኝና ልብ በሚሰብር ሁኔታ እየተሰቃየች ያለች ጨቅላ ወገናችንን ህይወት በቅንጭቡ የሚያሳይ ምስል ለተመለከተ:: ስሟ ማሾ ሁሴን ይባላል ከታናሽ ወንድሟ ጋር በጉዲፈቻነት የተሰጡት ከ ሁለት ዓመታት በፊት ሲሆን በጣም የሚያሳዝነውና የሚያስገርመው ወላጆቻቸው በህይወት የሚኖሩ መሆናቸው ነው:: ዛሬ ማሾ (ስምን መልዓክ ያወጣዋል ነው ወይስ ነበር) እንኳን ማሾ ሆና ለሌላው ብርሀን ልስትለግስ ቀርቶ ጋዟ አልቆባት ለመጥፋት ጭልጭል የምትል ኩራዝ መስላ ያ ፍልቅልቅ እና ሳቂታ የልጅነት ወዟ ተሟጦ ልቧ በናፍቆትና በሀዘን ተሰብሮ ዴንማርክ አገር በሚገኝ ወላጅ አልባ ህጻናት ማሳደጊያ ውስጥ ሳትወድ በግድ የመከራ ገፈት ከታናሽ ወንድሟ ጋር በመጋት ላይ ትገኛለች:: ወላጆቿ እሷንና ወንድሟን በጉዲፈቻነት እንዲሰጡ የተገደዱት በወቅቱ ሀኪማቸው በደማቸው
ውስጥ ኤችአይቪ ቫይረስ የተነሳ ከሁለት ዐመታት በላይ ሊቆዩ እንደማይችሉ ስለነገራቸው ለልጆቻቸው ደህንነትና ጥሩ ኑሮ እንዲኖሩ በማሰብ ነበር:: የተባለው እንደታሰበው ሳይሆን ቀርቶ የማሾ ሁለቱም ወላጆች በህይወት በመኖር ላይ ሲገኙ እነሱም በልጆቻቸው ናፍቆት እንዲሁም በህይወት እያሉ ልጆቻቸውን ለባእድ በመስጠታቸው ከፍተኛ የሆነ የጥፋተኝነት ስሜት እየተሰማቸው በመሰቃየት ላይ ይገኛሉ:: የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መ/ቤት ባለስልጣን አቶ አደራጀው እና የጉዲፈቻ ድርጅቱ ሰራተኞች ቃላቸውን በማጠፍ እነማሾ ስላሉበት ወቅታዊ ሁኔታ ለወላጆቻቸው ምንም አይነት መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል:: ማሾ እንኳን ሳይንቲስት ሆና አገሯንና እና ቤተሰቧን ልትጠቅም ቀርቶ በህይወትና በሞት መካከል ላይ ትገኛለች:: ማሾን እና ወንድሟን በጉዲፈቻነት ለማሳደግ የወሰዷቸው ዴንማርካውያን የልጆቹን ቁሳዊም ሆነ ሌሎች ፍላጎቶች ለማሟላት የሚቻላቸውን ቢጥሩም የወላጅን ፍቅርና ናፍቆት ለመስጠት ባለመቻላቸው ሁኔታው ከቁጥጥራቸው ውጪ በመሆኑ እዛው አገር ለሚገኝ የወላጅ አልባ ህጻናት ማሳደጊያ ድርጅት ለመስጠት ተገደዋል:: ማሾ እና ወንድሟ ከወላጆቾቻቸው ጋር በሚኖሩበት ጊዜ የሚተኙት ወለል ላይ: የሚበሉት ቁራሽ የዘንጋዳ ቂጣ: የሚለብሱት ጥብቆ ቢሆንም በወቅቱ ደስተኞች ነበሩ:: ዛሬ የራሳቸው ምቾት ያለው አልጋ: ጮማና መረቅ: ውድ መጫወቻዎችና ልብሶች ቢኖሩዋቸውም ደስታ ርቋቸው ከሰውነት ተራ ወጥተው ባህር አቋርጠው ከዚህ በፊት አይተው የማያውቁትን ምግብ:ባህል:የአየር ንብረት እንዲለምዱና እነሱ ባልመረጡት የህወት መንገድ እንዲጓዙ ተገደዋል:: ማሾ ዛሬ የሚያስፈልጋት እያንጎራጎረች ጸጉሯን የምትቆንናት እናት ትከሻው ላይ እንኮኮ አድርጎ የሚያጫውታት አባት እንጂ ሰው ሰራሽ የመዝለያ ትራምፖሊን: ኤክስቦክስ የቪድዮ መጫወቻ ወይም ባርቢ አሻንጉሊት አይደለም:: ሌሎች እንደማሾ ፍላጎታቸው ሳይጠየቅ በጉዲፈቻነት ተሰጥተው በአሜሪካ: በካናዳ በአውሮፓ እና በተለያዩ አገራት የስቃይ ገፈት በመጋት ላይ የሚገኙ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ጨቅላ ወገኖቻችንን ቤት ይቁጠረው:: ማሾ ሁሴንና እና ወንድሟ በዚህ ዐመት ላይ በጉዲፈቻነት ተሰጥታ አሜሪካን አገር በሚገኖሩ ወላጆቿ በደረሰባት ኢሰብአዊ እና ዘግናኝ ወንጀል ምክንያት ህይወቷን በለጋ እድሜዋ ያጣችውን የሀናን እጣ ፈንታ እንዳይደርስባቸው ከፈለግን:ነገ ዛሬ ሳንል እነዚህን ደጋፊም ሆነ አስታዋሽ የሌላቸውን ሁለት ምስኪን ወገኖቻችንን ከወላጅ አሳዳጊዎቻቸው ጋር ማገናኘት የሁላችንም የሰብዐዊነትና የዜግነት ግዴታ ሲሆን በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውናንና ህፃናትን በጉዲፈቻ ስም የመሸጥ ዘመቻ እንዲቆም ማድረግ የግድ ይለናል:: ልኡል አለማየሁ ቴዎድሮስ በስደት በሚኖርበት እንግሊዝ አገር በወላጅ ናፍቆት በ19 ዐመቱ ሲቀጠፍ ልንታደገው ያልቻልነው በወቅቱ እንዳሁኑ ምቹና ቀልጣፋ መገናኛም ሆነ ትራንስፖርት አለመኖሩን በማላከክ ሊሆን ይችላል ማሾንም ሆነ ሌሎች በተመሳሳይ ችግር ላይ የሚገኙ የመጪው ትውልድ ተረካቢዎችን ከልኡል አለማየሁ ቴዎድሮስ እጣፋንታ ላለማዳን ከቶ ምንም ምክንያት የለንም:: አዎ ከሰው ቤት እንጀራ ጮማና መረቁ የናት ቤት ይሻላል ዘንጋዳ መረቁ::
አበቃሁ

No comments:

Post a Comment