«....ማንም
ሰው ለመማርና ለመሠልጠን መድከም አለበት።» ዳግማዊ አጤ ምንሊክ ንጉሰነገስት ዘኢትዮጵያ
በ፲፰፻፺፰
ዓ.ም
ስለትምሕርት ያስነገሩት አዋጅ
«እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ በምቀኝነት እርስ በርሳችሁ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በቀር ኢትዮጵያን አገራችንን ለሌላ ለባእድ አትሰጧትም፤ ክፉም ነገር አገራችንን አያገኛትም። ነፋስ እንዳይገባባችሁ አገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ፤ ወንድሜ ወንድሜ እየተባባላችሁ ተደጋገፉ፤ የኢትዮጵያን ጠላት ተጋግዛችሁ ተደንበር መልሱ። የኢትዮጵያ ጠላት ባንዱ ወገን ትቶ ባንድ ወገን ቢሄድና ደንበር ቢገፋ፤ በኔ ወገን ታልመጣ ምን ቸገረኝ ብላችሁ ዝም አትበሉ፤ ያ ጠላት በመጣበት በኩል ኁላችሁም ሄዳችሁ አንድነት ተጋግዛችሁ ጠላታችሁን መልሱ እስከ እየቤታችሁ እስኪመጣ ዝም ብላችሁ አትቆዩ» ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ፤ ግንቦት ፲ ቀን ፲፱፻፩ ዓ.ም
ልክ በዛሬዋ እለት ከመቶ ዓመት በፊት እኝህ የኢትዮጵያንም ሆነ የመላው ጥቁር ዘር ታሪክ የቀየሩት እና ከዘመናቸው ቀድመው የተወለዱት ኢትዮጵያዊ መሪ ለዓመታት ሲታገሉት የነበረው ህመማቸው አሸንፏቸው እችን ዓለም ተሰናበቱ። ኢትዮጵያዊ ታሪክ ጸሃፊ መርስዔ
ኀዘን ወልደ ቂርቆስ -
ትዝታዬ
- ስለራሴ
የማስታውሰው ፲፰፺፩ - ፲፱፳፫ በሚለው መጽሃፋቸው ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በህልፈት ሲለዩ የነበረውን ሁኔታ በዚህ መልኩ ነበር የገለጹት፦
"በዚህ
ዓመት አጤ ምኒልክ ሕመም ጸንቶባቸው ነበርና
ታኅሳስ ፫
ቀን ፲፱፻፮ ዓ.ም.
በዕለተ
ዓርብ ሞቱ፡፡ ወዲያው እንደሞቱ የግቢ ሥራ
ቤቶች የልቅሶ ድምጽ አሰሙ፡፡ ነገር ግን የልጅ
ኢያሱ ባለሟሎች አገር እንዳይሸበር ሰግተው
በቶሎ ዝም አሰኟቸው፡፡ አቤቶ ኢያሱ በዚያ
ዕለት ያደሩት ፍልውሐ በሚባል በመታጠቢያ
ቤታቸው ነበር፡፡ እዚያው እንዳሉ ማለዳ
የአባታቸውን የአጼ ምኒልክን መሞት ሲሰሙ
ደንግጠው ወደ ቤታቸው ወጥተው ተቀመጡ፡፡
ሆኖም ሀገር እንዳይሸበር በማለት ኀዘናቸውን
በይፋ አላሳዩም፡፡ እንዲያውም አንዳች ኀዘን
አለመኖሩን ለማስመሰልና ለማሳመን ሲሉ በማግሥቱ
ቅዳሜ ወደ ጃንሜዳ ወጥተው ከአሽከሮቻቸው
ጋር በፈረስ ጉግስ ሲጫወቱ ዋሉ፡፡ ይህም
ለሀገር ጸጥታ ሲባል አማካሪዎች ያቀረቡላቸው
ዘዴ መሆኑ አይጠረጠርም፡፡ ስለዚህ የአጤ
ምኒልክ ሞት ሚስጥር ሆኖ ተደበቀ፡፡የአጤ
ምኒልክን አስክሬን አሽከሮቻቸው እንደ ነገሥታት
ማዕረግ አምሮ በተሠራ በብረት ሣጥን አድርገው
በቤተ መንግስቱ ግቢ ውስጥ ባለችው በሥዕል
ቤት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በክብር
አስቀመጡት፡፡ባለቤታቸው
እቴጌ ጣይቱና ልጃቸው ወይዘሮ ዘውዲቱ በሳጥኑ
አጠገብ ሆነው መሪር ልቅሶ ያለቅሱ ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ አጤ ምኒልክ በሕይወት አሉ እየተባለና
እየተወራ እስከ ሰገሌ ዘመቻ ድረስ ሁለት ዓመት
ከአሥር ወር ተደበቀ፡፡ የመንግሥቱ ሥራም
በስማቸው ይካሄድ ነበር፡፡ አጤ ምኒልክ
የተወለዱት ነሐሴ
፲፪ ቀን ፲፰፻፴፮ ዓ.ም. ስለሆነ
በሞቱበት ጊዜ ዕድሜያቸው ስድሳ ዘጠኝ ዓመት
ከአራት ወር ነበር፡፡"
ስለ ስማቸው አመጣጥ የሚያስረዳውን ታሪክ በመጀመሪያ እንመልከት። ይህ ጽሁፍ የተገለበጠው ከዊኪፒዲያ እንደሆነ በቅድሚያ አስታውቃለሁ።
ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ከአባታችው ከሸዋው ንጉሥ ኃይለ
መለኮት ሣህለ ሥላሴና ከእናታቸው ወይዘሮ
እጅጋየሁ ለማ አድያም ቅዳሜ ነሐሴ
፲፪ ቀን ፲፰፻፴፮
ዓ.ም.
ደብረ
ብርሃን አካባቢ አንጎለላ
ከሚባል ሥፍራ ተወልደው፤ በአንጎለላ
መቅደላ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን
ክርስትና
ተነሱ።
አያታቸው
ንጉሥ
ሣህለ ሥላሴ የልጁን መወለድ ሲሰሙ “ምን
ይልህ ሸዋ” በሉት ብለው ስም አወጡ።እሳቸው
“…ምኒልክ በሚል ስም የሚነግሥ ንጉሥ ኢትዮጵያን
ታላቅ ያደርጋታል” የሚል ትንቢት ስለነበር
‘ምኒልክ’ የኔ ስም ነው ብለው ነበር። ሆኖም፣
በህልማቸው ከልጁ ጋር አብረው ቆመው ከሳቸው
ጥላ የልጁ ጥላ በልጦ፤ በእግር የረገጡትን
መሬት ሲያለካኩ እሳቸው ከረገጡት ልጁ የረገጠው
ረዝሞ አዩ። ከዚህ በኋላ “ምኒልክ የኔ ስም
አይደለም። የሱ ነው። ስሙን ምኒልክ በሉት”
ብለው አዘዙ ይላል ጳውሎስ
ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በተባለው መጽሐፉ (ገጽ
፲፪)
አጤ ምኒልክ ለኢትዮጵያ ካበረከቱት እና ከሚመሰገኑባቸው ጉዳዮች አንዱ በወቅቱ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን መሪዎች እና ተከታዮች ተፈጥሮ የነበረው ልዩነት ወደ ግጭት እና ክፍፍል ሳያመራ በሰላም እንዲፈታ ከአጤ ዮሃንስ ጋር በመሆን ያደረጉት ያላሰለሰ ጥረት ይጠቀሳል። ብዝዎች እምዬ ምኒልክ እያሉ የሚያሞኳሻቸውን እኝህ ኢትዮጵያዊ መሪ ሌሎች ደግሞ ጨካኝ፡ወራሪ እና ተስፋፊ በማለት ያጥላሏቸዋል። ለእዚህ በምሳሌነት የሚያቀርቡት ደግሞ አጤ ምኒልክ በደቡብ፡ በምስራቅ እና ምዕራባዊ የሚገኙ ህዝቦችንና አካባቢዎችን ለማስገበር ያደረጓቸው ጦርነቶች እና ግጭት ዓልባ ሁነቶች ማለትም በጊዜው የነበሩ ባላባቶችን፡መሳፍንቶች እና የጎሳ መሪዎችን በአምቻ እና ጋብቻ ወደ እሳቸው መንግስት እንዲቀላቀሉ የተጠቀሙባቸውን ልዩ ልዩ እንደ ዓብነት ይጠቅሳሉ። ሌሎች በበኩላቸው ከአድዋ ጦርነት በኋላ ኤርትራን ከጣልያን ቅኝ ገዥዎች ነጻ እንድትወጣ ባለማድረጋቸው እና ጅቡቲን ለፈረንሳይ መንግስት በኪራይ መልክ ለመቶ ዓመት በመስጠታቸው ይኮኗቸዋል። አንድ መረሳት የሌለበት ነገር ግን በወቅቱ የነበረው የሃይል አሰላለፍ፡የሰራዊታቸው መዳከም እና የመንግስታቸው ለተለያዩ ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫና የነበረበት በመሆኑ አጤ ምኒልክ እነዚህ ስምምነቶች ሳይወዱ በግድ እንዲፈርሙ ግፊት እንዳደረጉባቸው በጂኦፖለቲካዊ እና
በታሪክ ተመራማሪዎች ዘንድ ይታመናል። አጤ ምኒልክ እነዚህን ርምጃዎች በወቅቱ ባይወስዱ ኖሮ አገሪቱ ወደከፋ የእርስበርስ ግጭት እና ብጥብጥ እሳቸውም የቀደምቶቻቸው ማለትም የአጤ ቴዎድሮስ እና አጤ ዮሃንስ እጣ ሊያጋጥማቸው ይችል እንደነበር ብዙ አመላካች ነገሮች ነበሩ። አጤ ምኒልክ ወደድንም ጠላንም ሰብዓዊ ፍጡር እንጂ መልአክ አልነበሩም። በዘመናቸው በነበረው ርእዮተዓለማዊ እና ፓለቲካዊ አስተሳሰብ አማካኝነት ለአገር እና ለህዝብ ይጠቅማሉ የሚሏቸውን ውሳኔዎች እና ርምጃዎች በመውሰድ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን መልክዓዊምድር አቀማመጥ እንድትይዝ እና በስልጣኔ በእድገት ጎዳና እንድትጓዝ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር አንጸባራቂ ገድል ነው። የመጀመሪያው ትምህርትቤት፤ሆስፒታል፤ባንክ፤ስልክ፤የባቡር ሃዲድ፤መኪና፤ሲኒማ ቤት፤ሆቴል፤ቧንቧ ውሃ፤የተከፈቱት በአጤ ምኒልክ ዘመን ሲሆን ልዩ ልዩ ዘመናዊ የሆኑ መንግስታዊ መዋቅሮች እንዲዘረጉ በማድረግ ፈር ቀዳጅ መሪ ነበሩ። እስኪ እንደማጠቃለያ በወቅቱ ለነበሩት የእንግሊዝ ንግስት አቻቸው ፎኖግራፍ በተባለ የድምጽ መቀረጫ የላኩትን የምስጋና መልእክት እናዳምጥ። ድምጹ ጥራት ስለሚጎለው የመልእክቱ ጽሁፍ ከታች ይገኛል። አሁን በስልጣን ላይ ያሉትም ሆነ መጭዎቹ ገዥዎቻችን የእኝህ ታላቅ መሪ ልቦናና አርቆአስተዋይነት ይስጣቸው። አሜን
«እኔ
ዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
እጅግ ለከበሩ ወዳጃችን ቪክቶሪያ የታላቅ
የእንግሊዝ ሕዝብ የሕዝብ ነገሥታት መድኃኔ
ዓለም ጤና ይስጥልኝ እላለሁ። በሙሴ
ሃሪንግቶን እጅ እጅግ የተዋበ ያማረ የንግሥት
ፎኖግራፍ ሲደርስልኝ የከበሩ ንግሥት ድምፅ
አጠገቤ ሆነው ስሰማ በብዙ ደስታ አደመጥኩ።
ለኛና ለመንግሥቴ ስለ መልካም ምኞትዎ እግዚአብሔር
ያመስግንዎ። ለርስዎ ዕድሜና ጤና ለሕዝብዎ
ሰላምና ዕረፍት እግዚአብሔር ይስጥዎ።
በሁለታችን ሕዝብ መካከል ያለውን ጉዳይ ሁሉ
ከሙሴ ሃሪንግቶን ጋር ተነጋገርኩ። እርሱም
አሁን ወደ እንግሊዝ አገር እመለሳለሁ ቢለኝ
ጉዳያችንን ሁሉ አቃንተህ ብትመለስ ደስ ይለኛል
ብዬ ነገርኩት። አሁን ደግሞ ንግሥት በደህና
እንዲቀበሉት። ደግሞ የመተማ ነገር የእኛ
ታላቁ ንጉሣችንና ብዙ የአገራችን ሰዎች
ስለኃይማኖታቸው እልህ ብለው የሞቱበትን
ለሙሴ ሃሪንግቶን ነግረነዋልና ይህንን ከተማ
የእንግሊዝ መንግሥት እንዲያውቅልን እርስዎ
ይረዱናል ብዬ ተስፋ አለኝ። ኢትዮጵያ እና
የእንግሊዝ አገር በሰላምና በፍቅር እንዲኖሩ
እግዚአብሔር ይርዳን ብዬ ለታላቅ ሕዝብዎ
የክብር ሰላምታዬን አቀርባለሁ።»
በይበልጥ ስለ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ታሪክ ማንበብ እና መረጃዎች ከፈለጉ እዚህ ጋር ይጫኑ። መልካም ንባብ
No comments:
Post a Comment