የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ወይም ሲፒጄ በሚል የምጽሃረ ቃል የሚጠራው ዓለምዓቀፉ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ተሟጋች ቡድን ትናንትናው እለት በድረገጹ ላይ እንዳስታወቀው፡ እነዚህ ሃያ የሚሆኑ በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚተዳደረው የኦሮሚያ ቴሌቪዥን ባልደረቦች ያለምንም ማስጠንቀቂያ ከስራ ገበታቸው የተሰናበቱ ሲሆን በዓሁኑ ሰዓት መንግስት በሰበብ አስባብ እንዳያስራቸው በመስጋት ተደብቀው እንደሚገኙ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ጋዜጠኛ ለሲፒጄ ከሰጠው ቃለመጠይቅ ለመረዳት ተችሏል። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጁን 25 እነዚሁ ሰራተኞች ወደ ቴሌቪዥን ጣቢያው መግባት እንደማይችሉ በስራ ሃላፊዎቻቸው እንደተነገራቸው ገልጸው፡ በምን ምክንያት ውሳኔው ሊተላለፍባቸው እንደተቻለ ምንም የተገለጸላቸው ነገር አለመኖሩን ለሲፒጄ አስታውቀዋል።
እንደሚታወቀው ባለፈው ሚያዚያ መንግስት ሊያጸድቅ ያቀደው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በዋና ከተማ ዙሪያ አካባቢዎች ላይ የሰፈሩ ገበሬዎችን ያፈናቀላል በሚል በተለያዩ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከፍተኛ የተቋውሞ ሰልፍ አስነስተው በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ከፍተኛ አደጋ ደርሶ ነበር። የኦሮሚያ ቲቪ ጋዜጠኞች ይህንን ፖሊሲ የሚተች ነው ያሉትን ዘገባ እና የገዥው ፓርቲ ባለስልጣናት የተሳተፉበትን ስብሰባ ከተቃውሞ ሰልፉ አንድ ቀን ቀደም ብለው ማቅረባቸው ከስራ ለመባረራቸው መነሾ ሊሆን እንደሚችል አክለው ገልጸዋል። ይህ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገው ጋዜጠኛ ለሲፒጄ በሚከተለው መልኩ ገልጾታል።
"መንግስት እሱ በሚፈልገው/በሚመርጠው አስተሳሰብ ሊያጠምቅህ ካልቻለ፡ ከስራ ገበታህ ያፈናቅልሃል"
የጋዜጠኞቹን መባረር ተከትሎ አቶ በረከት ስምኦን እና የፋና ብርድካስት በአዳማ ከተማ ባዘጋጁት ግምገማ የኦሮሚያ ጋዜጠኞች እንዲሳተፉ የተደረጉ ሲሆን፡ ዓላማው የጋዜጠኛውን ክህሎት እና የስራ ብቃት ለማጎልበት ሳይሆን የጋዜጠኞቹን የፖለቲካ አቋም ለመሰል የተሸረበ ሴራ እንደነበረ፡ በዚሁ ግምገማ ላይ የተሳተፉ ጋዜጠኞች ተናግረዋል። ግምገማውን ያዘጋጁት አንዳንድ ካድሬዎች ለጋዜጠኞቹ እንዳሰረዱት፡ የተቋውሞ ሰልፉን በተመለከት የኦሮሚያ ቲቪ ሲያቀርቡት በነበረው ዘገባ ላይ መንግስት ደስተኛ እንዳልነበር ነው።
እንደሲፒጄ ዘገባ፡ እነዚህ ከስራ የተባረሩት ጋዜጠኞች ከአምስት ዓመት በላይ የስራ ልምድ እንዳላቸው ለመረዳት ተችሏል።
ምንጭ ሲፒጄ
No comments:
Post a Comment