ቁጥራቸው
ከሶስት መቶ በላይ የሚሆኑ በስዊድን የሚኖሩ
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዛሬ
ህዳር አራት ሁለት ሺህ ስድስት በዋና ከተማዋ
ስቶክሆልም በሚገኘው የሳውዲ አረቢያ ኤምበሲ
ፊትለፊት በመገኘት በሳውዲ ዓረቢያ ከአምስት
ቀናት በፊት በኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸን
ላይ እየተባባሰ የመጣውን ኢሰብዓዊ እና ጨካኝ
ድርጊት በመቃወም ቁጣቸውንና ተቋውሞቸውን
አሰሙ። እንደ ኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር
ከቀኑ በሰባት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት በዘለቀው
በዚህ በዓይነቱ ልዩ እና ደማቅ በሆነውተቋሞ
ሰልፍ ላይ ኢትዮጵያውያን ዘር፡ሃይማኖት፡እና
የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድባቸው የተገኙ ሲሆን
የተለያዩ መፈክሮችን እና የኢትዮጵያን ሰንደቅ
ዓላማ በመያዝ የሳውዲ መንግስት ይህን
በኢትዮጵያውያን ላይ ያነጠጣረ እና በዘረኝነት
ላይ የተመረኮዘ እጅግ አሰከፊ በደል እና
የዓለምዓቀፍ ሰብዓዊ ድንጋጌዎችን የጣሰ
ወንጀል በአስቸኳይ እንዲያቆም እና ወንጀለኞቹም
ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል። በእለቱ ከተቋውሞ
ሰልፉ አዘጋጆች የቀረበውን ደብዳቤ የኤምበሲው
ባለስልጣናት አንቀበልም በማለታቸው፡ የተቋውሞ
ሰልፈኞቹ ቁጣቸውን "ተከብረሽ
የኖርሽው ባባቶቻችን እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ
ይውደም"
የሚለውን
ቀስቃስሽ ዜማ በአንድነት በመዘመር ገልጸዋል።
በወቅቱ ሲያሰሙ ከነበሩት መፈክሮች መካከል
ፍትህን እንሻለን፡ እህቶቻችን አስገድዶ
መድፈር ይቁም፡ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን
ማሰቃየት እና መግደል
በአስቸኳይ ይቁም የሚሉ ይገኙበታል። ከዚህ በተጨማሪም ጉዳዩ በቀደምትነት የሚመለከተው የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ በሳውዲ የሚገኘው ኤምበሲ ይህንን በኢትዮጵያውያን ወገኖች ላይ በመፈጸም ላይ ያለውንና ከእለት ወደእለት እየተባባሰ የመጣውን ግፍ እንዲቆም አንዳችም ጥረት አለማደረጉ በእጅጉ እንዳሳዘናቸውና እና እንዳስቆጣቸው ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ገልጸዋል። በሰልፉ ማብቂያ ላይም፡ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ በተለያዩ የሳውዲ ከተሞች ህይወታቸውን በግፍ ላጡ ወገኖቻችን የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት አድርገዋል። ካለፉት 5 ቀናት ጀምሮ በሳውዲ አረብያ በተለያዩ የማጎሪያ ጣቢያዎች ታስረው በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ እንደቀጠለ ሲሆን፣ እሰካሁን ድረስ 2 ሰዎች መሞታቸው ታውቋል። ኢትዮጵያውያኑ እንደሚናገሩት ሰዎቹ የተገደሉት ባልና ሚስቶችን ለመለያየት በተደረገ ሙከራ ላይ በተፈጠረ ግርግር ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩ ረግቧል በማለት መግለጫ ቢሰጥም በሳውዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ግን ችግሩ አሁንም በአስከፊ ሁኔታ መቀጠሉን ተናግረዋል። በሪያድ የሚኖር አንድ ኢትዮጵያዊ ለኢሳት እንደገለጸው አብዛኛውን ኢትዮጵያውያንን ከከተማ በማውጣት በረሀ ውስጥ አጉረዋቸው እንደሚገኝ ገልጿል።
No comments:
Post a Comment