ዛሬ ይለያል ጉዱ
እስቲ በትልቁ ወንድም አፍሪካ በእንግሊዘኛው አጠራር ቢግብራዘርአፍሪካ ልጀምር። ይህ በጂዮርጅ ኦርዌል ልብወለድ መጽሃፍ ላይ ከሚገኝ አንድ አምባገነን ገጸባህሪ ስሙን በውሰት በመውሰድ በሆላንድ አገር እንደ አውሮፓውያኑ ቀመር በ1990 መጨረሻ ላይ የተጀመረ Reality Show የቴሌቪዥን የመዝናኛ ይቅርታ የመጃጃያ ዝግጅት አገር፡ድንበር እና ባህር በማቋረጥ በመላው ዓለም ታዋቂነትን በማግኘት ወደ አፍሪካ በመዝለቅ ከደቡብ አፍሪካ ለአፍሪካውያውን አድናቂዎች ዝግጅቱን ማሰራጨት ከጀመረ እነሆ አንድ አስርት ዓመት ሆኖታል። እኔ በበኩሌ ይህንን ዝግጅት ተከታትዬው የማላቅ ሲሆን ዛሬ ይሄን ጦማር እንድጦምር ያነሳሳኝ ግን ባለፉት ሳምንታት ኢትዮጵያ ውስጥ እና በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ከሆኑት ጉዳዮች አንዷ
ቤቲ የተባለች የዚህ ዝግጅት ተሳታፊ በመሆኑዋና ትናንት በተደረገው ምርጫ ከውድድሩ እንዲሰናበቱ በተወዳዳሪዎች ድምጽ እንዲሰጥባቸው ከተወሰነባቸው ተወዳዳሪዎች መካከል ይህችው ኢትዮጵያዊት አንዷ በመሆኗ ነው። ምንዓልባት ለዚህ የቴሌቪዥን ዝግጅት እንግዳ የሆናችሁ ካላችሁ የዝግጅቱ ይዘት ከአገር አገር እና ክፍለ ዓለም በተለያየ መልኩ ቢለያይም ጠቅለል ባለ መልኩ ይሄን ይመስላል። በዚህ ቢግብራዘርአፍሪካ በተባለው ዝግጅት ላይ የሚሳተፉት በዓብዛኛው በ 20ዎቹ እና 30ዎቹ የእድሜ ክልል የሚገኙ ከዚህ በፊት በአካል ተገናኝተው የማያውቁ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ወጣት ሴቶችና ወንዶች ሲሆኑ፡ ለሶስት ወራት ያህል ከውጭው ዓለም ተገልለው በአንድ ጣራ ስር በመሆን እያንዳንዱ እንቅስቃሲያቸው ሌት ተቀን፡ብርሃን ከጨለማ በማይበግራቸው ካሜራዎች ቁጥጥር ስር እየተቀዳ የተለያዩ ውድድሮችን በማድረግ በመጨረሻም አሸናፊው ግለሰብ ወይም ግለሰቦች የ ሶስት መቶ ሺህ የአሜሪካን ዶላር ተሸላሚ ለመሆን የሚያስችል ነው። በዚህ በሶስት ወር ቆይታቸው በመጀመሪያዎቹ ዙሮች ተሳታፊዎች እንዲባረሩ የሚፈልጓቸውን ሰዎች ከመረጡ በኋላ ብዙሃኑ የመረጠው/የመረጣት ተወዳዳሪ ከውድድሩ የሚሰናበት ሲሆን በመቀጠልም ተመልካቾች በሚሰጡት ድምጽ ብልጫ አማካኝነት ከውድድሩ በተለያዩ ጊዚያት ተሳታፊዎች እየተወገዱ ፍጻሜ ላይ በመድረስ ውድድሩ ይጠናቀቃል። ከኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ዝግጅት የተሳተፈው ግለሰብ በ 2009 እንደ ዓውሮፓውያኑ ቀመር ሲሆን በዚህ ዓመቱ ዝግጅት ላይ ደግሞ ቤቲ የተባለችው መምህርትና የሃያ ስድስት ዓመቷ ጉብል ተካፋይ ሆና በውድድሩ ላይ የመቆየቷ እጣ ፋንታ በትናንትናው ምሽት የታወቀ ሲሆን ከዚህ ውድድር መሰናበቷ ይፋ ሆኗል። ወደ አገሯ ስትመለስ የሚደረግላት አቀባበልም በውል አለየም። እንደማርያም ጠላት በድንጋይ ወይስ እንደ ጀግና በአበባ እና እልልታ የሚለውን እስቲ ወደ ፊት ይታያል ግን ቤቲን ለዚህ የሚያበቃ ምን ጉዳይ ፈጸመች
ቤቲን ለቀቅ
ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ይህንን የቴሌቪዥን ዝግጅት የማልከታተል ሲሆን ምክንያቶቼም ግላዊ እና ይዘቱ እጅግ በጣም ስለማይስማማኝ ሲሆን በተለይም እዚህ ስዊድን አገር እንደመጣሁ ያየኋቸው በጣት የሚቆጠሩ ዝግጅቶች ላይ ያየኋቸው ነገሮች በጭራሽ አእምሮዬ ሊቀበላቸው ስላቻለ ነው። ሰሞኑን ግን ቤቲን አስመልክቶ በተለያዩ የመገናኛና ብዙሃን እና የማህበራዊ አውታሮች በከፍተኛ ሁኔታ መነጋገሪያ መሆኗ ለዚህ ጦማር እንደመንደርደሪያ ሆኖኛል። አንዳንዶች ይባስ ብለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አመራር አካላት ከፊፋ የደረሳቸውን ምንያህል የተባለው ተጫዋች ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር በምታደርገው ጨዋታ ላይ እንዳይሳተፍ የሚያሳስበውን ደብዳቤ እንዲዘናጉ ያደረገቻቸው ቤቲ እንደሆነች ሁሉ በቀልድ መልክ ሲዘባበቱ ተስተዉሏል። በዚህ ዝግጅት ላይ ለመሳተፍ ምን ዓይነት መስፈርት እንዳለ ባላውቅም ተወዳዳሪዎቹ ግን የሚወክሉት ራሳቸውን እንጂ የመጡባቸውን አገሮች እንዳልሆነ ነው የማምነው። ለምን ቢባል ውድድሩን አሸንፈው የገንዘብ ሽልማቱን ቢያገኙ የአገራቸው ሰንደቅዓላማ እየተውለበለበ ብሄራዊ መዝሙር አይዘመርላቸውም፡ ይህ ሆኖ ሳለ በጣም ቁጥር ስፍር የሌላቸው በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም አንዳንድ ጋዜጠኞችና የማስታወቂያ ባለሙያዎች ቤቲ በዝግጅቱ ላይ ፈጸመች በተባለው ድርጊት አገሯን እንዳዋረደች በማራገብ እና በማጮህ እሷን እና ቤተሰቧን መነጋገሪያ እና መጠቋቀሚያ አድረገዋት ሰንብተዋል። በዚህ ለሶስት ወር በሚቆይ ዝግጅት ላይ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች እስከዝግጅቱ መጨረሻ በመቆየትና ሽልማቱን ለማግኘትና ላለመባረር ሲሉ ብዙ ውጣ ውረዶችን፡ ውድድሮችን ማለፍ ሲኖርባቸው በሂደቱ አንዳንዶቹ በአቻ ተወዳዳሪዎቻቸውም ሆነ በተመልካቹ ህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነትን ወይም ድምጽ ለማግኘት የተለያዩ ተቀባይነት ያላቸውንም ሆነ የሌላቸውን ድርጊቶች በማወቅም ሆነ በየዋህነት ሲፈጽሙ ማየት አንዱ የዝግጅቱ አካል ነው። እንግዲህ ቤቲ እንደዚህ ለውግዘት እና ለመነጋገሪያነት ያበቃት ከአንዱ የዝግጅቱ ተሳታፊ ጋር ስታደርግ ታየች የተባለው የአልጋ ላይ ጨዋታ ሲሆን፡ እኔ የተባለውን ድርጊት አለማየቴ ይታወቅልኝ። ቤቲ ይሄን ድርጊት አድርጋውም ከሆነ በተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ግፊቶች ወይም እያንዳንዱ በዛ ቤት ውስጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ በካሜራ እንደሚቀረጽ በመዘንጋት ሊሆን ይችላል የሚል የራሴ ግምት ሲኖረኝ እሷ አደረገች ከተባለው የባሰ አሰከፊ ድርጊቶች በማየቴ ምክንያት ነው ይሄንን ዝግጅት ከገና ከጅምሩ ማየት የተውኩት።
እና ምን ይጠበስ
ይሄ ቤቲ ፈጸመች የተባለው ድርጊት ግን ወንጀሉ ምን ላይ እንደሆነ እና ለምን እሷና ቤተሰቧ በዚህ መልክ ሊብጠለጠሉ እንደቻሉ እስካሁን ድረስ እንቆቅልሽ ሆኖብኛል። አቶ ዓለምነህ ዋሴ የተባሉ ልማታዊ የማስታወቂያ ባለሙያ ለአንድ ከአዲስአበባ ለሚሰራጭ የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ በሰጡት ቃለምልልስ የቢግብራዘር ዝግጅትን በደንብ እንደሚከታተሉ እና እሳቸው የማያውቋት ቤቲ በዚህ ዝግጅት ላይ እንድትሳተፍ መደረጉ ትልቅ ስህተት መሆኑን በመጠቆም በሷ ምትክ ልማታዊ የሙያ አጋራቸው የሆኑትና እድሚያቸው ከ40ዓመት በላይ የሚገመተው ወ/ሮ ሙሉዓለም ታደሰ ቢሳተፉ ኖሮ ኢትዮጵያን ከውርደት ያድኗት እንደነበር ገልጸዋል። እስኪ አስቧቸው ወ/ሮ ሙሉዓለምን እና እነዛን በዓፍላ እድሜ ላይ የሚገኙ እና ልጆቻቸው ሊሆኑ ከሚችሉ አስራ ምናምን ሴቶችና ወንዶች ጋር ለሶስት ወራት ከዛች ቤት ሳይወጡ ምን የመሰለ ልማታዊ ማስታወቂያ ይዘውልን እንደሚመለሱ ሳሰበው ሃሃሃ እንዲህ ዓይነቱስ ዝግጅት ቢኖር እኔም አይመልጠኝ። ግን ግን፡ለመሆኑ አገራዊ በሆኑ ሌሎች እጅግ በጣም አንገብጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለምሳሌ በቃሊቲ እና በሌሎች ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ እስርቤቶች ባልሰሩት ወንጀል ስለሚማቅቁት በሺህ የሚቆጠሩ የህሊና እስረኞች፡ በዋና ከተማዋ አዲስአበባ እና በሌሎች ትልልቅ ከተሞች በሚገኙና እንደአሸን በመፍላት ላይ በሚገኙት የራቁት ዳንስቤቶች አንቱ በተባሉ የመንግስት ባለስልጣናት፡ ባለጊዜዎች፡ ባለገንዘቦች፡ እና የውጭ አገር ዜጎች በወሲብ ማብረጃነት በየምሽቱ ለጋ ና እምቡጥ ገላቸው ስለሚቸረቸረው ኢትዮጵያውያን ህጻናት አልያም ደግሞ በተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ቀን ከሌሊት ፍዳቸውን ስለሚያዩት በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ምነው ይሄን ያህል አልጮህን። ይህን ያህል የአገር ፍቅር ካለን ምነው በመላው አገሪቱ እንደ አሸን የፈሉት የጉዲፈቻ ድርጅቶች ደላሎች እና የመንግስት ካድሬዎች ኢትዮጵያውያን ጨቅላ ህጻናትን ከደሃ ወላጆች ጉያ በተለያየ መንገድ በመነጠል እንደሸቀጥ ለአውሮፓውያንና እና ሰሜን አሜሪካውያን በመሸጥ ኪሳቸውን በማደለብ እነዚህን ህጻናት ለመከራ ለስቃይ እንዲሁም ለሞት እንዲዳረጉ እያየን ለምን እንዳላየን ሆነን። ደርሶ የባህል ተሟጋች መሆን አዛኝ ቅቤ አንጓችነት እንጂ ሌላ ምን ሊባል አይችልም።ቤቲ ፈጸመች የተባለውን ብታደርግ እንኳን እድሜዋ የሚፈቅደውንና በራሷ ፈቃደኝነት ሲሆን ለውግዘት እና ለወቀሳ የሚያበቃ ነፍስ አላጠፋችም፡ አልሰረቀችም። ቤቲ እምትወክለው ራሷን ብቻ ሲሆን እንደማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር በአካሏ የፈቀደችውን ለማድረግ ተፈጥሮአዊ/ህጋዊ መብቷ ነው። በእርግጥ ስለ አገራችን ክብር የምንቆረቀረቆር ከሆነ መወያያት እና መነጋገር ያለብን አራት ኪሎ ምንይልክ ቤተመንግስት ላለፉት ሃያሁለት ዓመታት እንዳሻቸው ስለሚነዱን ገዥዎቻችንና እየተባባሰ ስለመጣው ዋልጌነታቸው፡የሰብዓዊ መብት ጥሰታቸው፡ሙሰኝነታቸው፡ግለኝነታቸውና አልጠግብ ባይነታቸው መሆን ይኖርበታል። ከዛ ውጭ ግን ቤቲንም ሆነ ቤተሰቧን ለማብጠልጠል ሞራላዊም ሆነ ህጋዊ ብቃት የለንም። ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት ቢኖር ድንጋይ አነስቶ ይውገራት አይደለምን መጽሃፉስ የሚለው፡፡ አበቃሁ
No comments:
Post a Comment