እንዴት ከረማችሁ?
ያለፈው ሳምንት እንዴት ነበር የእናንተን እንጃ የኔ ግን ለየት ያለ ነበር? ከባድ ሃዘን ላይ ነኝ መቼም በተከበሩ ጠቅላይ ምንስትራችን ላይ የወረደውን መከራ ያየ አገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ በሙሉ (ይሄ እነዚህ በአውሮፖ እና አሜሪካ የጠቅላይ ምኒስትራችንን እግር እየተከተሉ ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉ ጸረ ልማት እና ዲሞክራሲ ተቃዋሚዎችን አይመለከትም) ቢያንስ ቢያንስ ሰባት ቀን እንዳገራችን ባህል ፍራሽ መሬት አውርዶ በመተኛት፡ከል በመልበስ የአገራችንን በምግብ ራሳችንን የመቻል ስኬት ልምድ ለመጋራት በሄዱበት ወቅት ክብርና ዝናቸው በአንድ አሸባሪ ጋዜጠኛ አማሪካን አገር ውስጥ መገፈፉን በመቃወም ልማታዊ ሃዘኑን መግለጽ አለበት።
ታሪኩ እጅግ አሳዛኝ ስለሆነ ጽሁፉን ማንበብ ከመጀመራችሁ በፊት ባጠገባችሁ የጨርቅ ወይም ወረቀት እንባ ማበሻ ብታዘጋጁ የሚመረጥ ሲሆን አኬልዳማ ድራማን እንዲያዩ ያልተፈቀደላቸው ህጻናትም ባካባቢው ባይኖሩ ተመራጭ ነው። በሉ እንግዲህ ተዘጋጁ። በመጀመሪያ ከዚህ በታች ያለውን ጥቅስ ልተርጉምና ወደ ዝርዝሩ የሃዘን ዜና እገባለሁ። የሚከተለውን ጥቅስ የተወሰደው አምባገነኖችን ማሸነፍ፦በአፍሪካና በመላው የሚገኙ አምባገነኖችን መታገያ ከተባለው በእውቁ የጋና ኢኮኖሚስት ፕሮፌሰር ጂዮርጅ አዬቴ ከተጻፈው መጽሃፍ ሲሆን ጥሬ ትርጉሙም እንደሚከተለው ነው። እጅግ የተከበረ አምባገነን መሪ የለም፧ ጥሩ አምባገነን መሪ የሞተው ብቻ ነው። “There is no benevolent dictator. The only good dictator is a dead dictator”.*
አያችሁት ፊልሙን አይደል? እስኪ ምን ባጠፉ ነው የተከበሩና የተወደዱ መሪያችን ይሄ ሁሉ ውርጅብኝ በመላው ዓለም ፊት ለዛውም አማሪካን አገር ውስጥ የሚወርድባቸው። እርግጥ ነው ካለፈው ዓመት መጋቢት ጀምሮ ለእኛ ደህንነትና ስጋት በመቆርቆር ከመቶ አስራ አራት ምናምን በላይ የሚሆኑ አሸባሪ ጋዜጠኞችንና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን፡አባሎችንና ደጋፊዎችን በማሰር እና እንዲቀጡ በማድረግ ከመቼውም በበለጠ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ያለምንም ፍራቻ የመንቀሳቀስና ሃሳባቸውን የመግለጽ መብታቸው እንዲረጋገጥ አድርገዋል። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ለም መሬቶች ላይ ሰፍረው የሚገኝ ወገኖቻችን በማፈናቀል መሬታቸውን ለውጭ ዜጎች እስከ መቶ ዓመት በሚደርስ በማከራየት በአረብ በቻይናና በሌሎች የኤጅያ አገራት የሚገኙ ህዝቦች ምግብ በርካሽ እንዲያቀርቡ መርዳትስ ምን ወንጀል አለው። የአሜሪካው ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማም የተከበሩ ምኒስትራችንም የጋበዙበት ዋናው ዓላማ ይሄ ነበር። እኛም ይሄንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተሰማንን ደስታ ለመግለጽ ድጋፋችንን በተለያየ መንገዶች ስንገልጽ ብንቆይም አንዳአንድ የግብዣው ዓላማ ያልገባቸው ኢትዮጵያውያን ይሄን በመቃወም ሃዘናቸውንንና ቁጣቸውን ሲገልጹ ታይተዋል። መቼም ከሰው ስህተት ከአምባገነኖች ውሸት አይጠፋም የሚለውን አገራዊ ብሂል በመንተራስ ነገርግን ይሄን ፊልም ከተመለከትን በኋላ ድጋፋችንን በተቋውሞ ለመግለጽ እንደተገደድን ለማሳወቅ እንወዳለን።
ምንአልባት ዘገባውን ያልተከታተላችሁ ካላችሁ ጉዳዩ የተፈጸመው አማሪካን አገር ሮናልድ ሬገን አዳራሽ ውስጥ ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ላይ የምግብ ዋስትናን በተመለከተ በተካሄደው ዓለምዓቀፍ ስብሰባ ላይ ሲሆን የዚህ እኩይ ዓላማ ፈጻሚም አበበ ገላው የተባለውና በአሸባሪነት ተከሰው በአማሪካን አገር ከሚኖሩት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነው። መቼም እንዲህ ዓይነቱን ጸያፍ እና የጠቅላይ ምኒስትራችንን ክብር የሚያዋርድ ተግባር በመላው ዓለም የሚገኝ ኢትዮጵያዊም ሆነ የሌላ አገር ዜጋ ነጻነት እና ዴሞክራሲ ወዳድ ህዝብ በቸልታ እንደማይመለከተው ጥርጥር የለኝም።
እንዴ መዲናችን ላይ ቀደም ሲል በተካሄደው የዓለም የምጣኔሃብት ስብሰባም ላይ እኮ ሊቁ ጠቅላይ ምኒስትራችን አስረግጠው የተናገሩት የምጣኔ ሃብት እድገት ከዴሞክራሲ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ነው። በፈረንጅ አፍ ለታዳሚዎቻቸው የተናገሩትን እንደሚከተለው ተርጉሜዋለሁ ዴሞክራሲና የምጣኔ ሃብት እድገት በታሪክም ሆነ በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ምንም ዓይነት ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት የላቸውም። እኔ ምጣኔ ሃብትንና ዴሞክራሲን በሚያያዙ የምሽት ተረቶችም ሆነ እሰጥ አገባዎች አላምንም። “There is no direct relationship between economic growth and democracy, historically or theoretically, I don’t believe in bedtime stories, contrived arguments linking economic growth with democracy.” ታዲያ ይህን የመሰለ ታሪካዊ እና እጅግ የበሰለ ንግግር መናገር ሊያስከብር እና ሊያስወድስ ሲገባ በመላው ዓለም ፊት ማዋረድ እንኳን ሰባት ቀን አንድ ዓመት ሃዘን አያስቀምጥም ትላላችሁ?
መቼም ያቺን በመሪያችን ላይ የደረሰውን 50 ሰከንድ ፊልም ያየ የዓለም ህዝብ ላለፉት 20 ዓመታት እኛ ኢትዮጵያውያን በምን ዓይነት ነጻነት እና ክብር እንደምንኖር ይገነዘባል ብዬ እገምታለሁ። እኔ መቼም እስካሁን ድረስ ይሄን በመሪያችን ላይ የደረሰውን ውርጅብኝ ለማመን በጣም ተቸግሪያለሁ፡ ደግሞ እኮ ካልጠፋ ቦታ በበጸረ ሽብር አጋራችን አማሪካን።ሌላ እንኳን ቦታ ቢሆን አይገርመኝም። ይሄ አሽባሪ ጋዜጠኛ መሪያችንን አሸባሪ፡ገዳይ፡ከማለት አልፎ የሱ ቢጤ አሸባሪ የሆነው እና በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንዲፈታ ከመጠየቅ አልፎ ከምግብ ዋስትና እኩል ኢትዮጵያውያን ነጻነት እንደሚያስፈልገን መድረኩን በመዳፈር ሲናገር መስማቴ ሃዘኔን እጅግ በጣም ከፍ አድርጎታል። በመላው ዓለም ውስጥ ከሚኖሩ ህዝቦች ከኢትዮጵያውያን ውጭ የየትኛው ሃገር ህዝብ ነው በነጻነት፡በእኩልነት፡በብልጽግና፡በወንድማማችነት/እህትማማችነት ያለፍርሃትና ጭንቀት፡ያለሃሳብ፡ የሚኖር? ይሄ ባለፉት ሃያ ዓመታት ከመቼውም በላይ ዜጎች
በነጻ የመናገር፡ የመጻፍ፡የመሰብሰብ መብቶች እና የፍትህ የበላይነት የተረጋገጡበት፡ እንደሆነ ማንም የሚክደው ሃቅ አይደለም።
ከዛሬ 15 ዓመት በፊት (ዓቤት ግዜው እንዴት ይሮጣል) የተወደዱ መሪያችን በአንድ አጋጣሚ ዋናው ህልማቸው ከ10 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያውን በቀን 3 ጊዜ ምግብ እንዲመገቡ ማስቻል መሆኑን ተናግረው ይሄው ህልማቸው ዛሬ እውን ሆኖ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ 99% የሚሆነው ብል ይቀለኛል ቁምራ (ቁርስ ምሳ ራት) የሚባለው የምግብ መርሃ ተጠቃሚ ማድረግ ማለትም ቢያንስ በቀን 1 ጊዜ ካልሆነም ጾሙን እንዲያድር ማስቻል እንግዲህ ምኑ ላይ ነው ሃጥያቱ?
ከዓመታት በፊት አሜሪካዊው ፕሬዚደንት ፊትዝጌራል ዲ ሩዝቬልት እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ 1937 እስከ 1956 ዓ᎐ም᎐ ኒካራጉዋን አንቀጥቅጦ ሰለገዛው አምባገነን መሪ አስመልክተው ተናገሩ እየተባለ የሚጠቀስ ጥቅስ አለ (ምንም እንኳን በእርግጥ እሳቸው እንደተናገሩት ማስረጃ ባይኖርም)፦ "
Anastasio Somoza (Nicaragua's dictator from 1937-1956) may be a son of a bitch, but he's our son of a bitch ” አናስታሲዮ ሶሞዛ መልቲ ሊሆን ይችላል፤ ያም ሆነ ይህ እሱ የእኛ የግላችን መልቲ ነው። ምን ለማለት ነው ሶሞዛ ለዜጎቹ መጥፎ መሪ ሊሆን ይችላል ቢሆንም የእኛን ጥቅም እስከጠበቀ እና እስካልነካ ድረስ ጉዳያችን አይደለም። መቼም የእኛን መሪ በአምባገነንነት የሚያማማቸው የለም፦ ለዚህም ይመስላል ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ አፍሪካ ውስጥ ከሚገኙ መሪዎች ሁሉ መርጠው ለዚህ ክብር ያበቋቸው።
ይሄንን በተመለከተም የአሜሪካው ፕሬዚደንት እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ 2009 ዓ᎐ም᎐ ለጋና የምክርቤት አባላት ባደረጉት ንግግር የሚከተለውን ብለው ነበር፦Africa doesn't need strong men, it needs strong institutions. አፍሪካ የሚያስፈልጓት ጨካኝ መሪዎች ሳይሆን ጠንካራ ተቋማት ነው። ድንቅ ብሂል። ለዚህም ይመስላል በኢትዮጵያ ከውጭ የሚገኝ የምግብ እህል እርዳታ ለዜጎች ያለምንም አድሎ የሚከፋፈለው፡ አቶ መለሰ ዜናዊ የሚመሩት የኢህአዴግ ፓርቲ ደግሞ በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2010 ዓ᎐ም᎐ በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ 99% የሚሆነውን የምክር ቤት ወንበር ጠቅልሎ የያዘው።
እናም ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባም ሆኑ ሌሎች የምስራቁም ሆነ የምዕራብ ዓለም መሪዎች እባካችሁ የተወደዱና የተከበሩ ጠቅላይ ምኒስትራችንን በቡድን 8ም ሆነ በሌሎች ስብሰባዎች ላይ እየጋበዛችሁ መሪያችንን እንዳታሳጡብን በመጠየቅ በዚህ ያልታሰበ ድንገተኛ ድርጊት ለተደናገጡት ውዱ መሪያችን እና ተከታዮቻቸው መጽናናትን ወንጀለኛው እና አሸባሪው አበበ ገላው አሜሪካ ዩሮፕ እና በመላው ዓለም እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኙ ተከታዮቹ እኛ ከእናንተና ከ እንግሊዝ መንግስት ቃል በቃል ተርጉመን ባዘጋጀነው የጸረ ሽብር ህግ ተዳኝተው ለፍርድ እንዲቀርቡ እንማጸናለን።
ፊርማ የማይነበብ
ከአምባገነኖች የጸዳ ዓለም፣አሜን!!!
No comments:
Post a Comment