Sunday, May 18, 2014

የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን እና የሶስቱ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች የቅዳሜና እሁድ ውሎ በህውሃት የካንጋሩ ፍርድቤት

ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ በአራዳ ምድብ ችሎት በአካል በመገኘት እንደዘገበችው እንደዘገበችው  በዛሬው እለት የተከናወነው   የፍርድ  ቤት ድራማ ያው ህውሃት እንደለመደው በፍቃዱ ሃይሉ ማህሌት ፋንታሁን እና አቤል ዋበላ ላይ ፖሊስ ከትላንትናው ጋር ተመሳሳይ የሆነ የ28 ቀን ጊዜ ቀጠሮ የጠየቀ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ 14 ቀን ፈቅዶለታል፡፡ፖሊስ የጸረ ሽብር አዋጁን በመጥቀስ በሽብር ክስ ለማቅረብ ስላሰበ 28 ቀን እንዲሰጠው የጠየቀ ቢሆንም ዳኛያለምንም የተለየ ተጨማሪ ነገር ከመነሻ ጥርጣሬ ለመቀየር ፖሊስ አሳማኝ ምክንያት ባለማቅረቡ 14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ብቻ ፈቅደዋል። የዛሬውን ውሎ ለየት የሚያደርገው፡ ፖሊስ የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች እና ወዳጆችን እንዳያለቅሱ፡ለታሳሪዎቹ እጃቸውን 
እንዳያውለበልቡ እና ምንም ዓይነት ምስል በፍርድቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳያነሱ/እንዳይቀርጹ መከልከሉ የአፈናውን 
መጠነሰፊነት ያሳያል። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ በትዊተር ላይ ዜጎች በሚከተለው መልኩ ቁጣቸው እና ሮሮአቸውን ሲገልጹ ነበር።


ህውሃት ኢትዮጵያውያንን መከልከል የቀረው መተንፈስ ብቻ ሳይሆን አይቀርም፡ ይሄንኑ በተመለከተ ደግሞ አንድ ፓሊኩ   የተባሉ ሚከተለው መልኩ ገልጸውታል









ቀኑ ቅዳሜ በመኾኑ ፒያሳ በሚገኘው የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ግቢ ውስጥ ከዘጠኙ ተጠርጣሪ ቤተሰቦች ውጪ መደበኛ ችሎት ሊከታተል የመጣ ሌላ ሰው አልነበረም፡፡ ከሁለት ሰአት ተኩል ጀምሮ ሲጠራቀም የቆየው የችሎት ተከታታይ ቀስ በቀስ በርከት ብሎ በግቢው መታየት ጀመረ፡፡ከጠዋቱ አራት ሰዓት ሲኾን ወደ ሰባት የሚሆኑ የታጠቁ ፌደራል ፖሊሶች አስቀድመው ወደ ግቢው በመግባት ግራ ቀኝ የቆመውን የእስረኞች ቤተሰብ፣ወዳጅ ዘመድ፣የአገር ውስጥና የውጭ አገር ብዙኃን መገናኛ ጋዜጠኞች፣ የአሜሪካ ኤምሲና የሌሎች አገራት ዲፕሎማቶች ወደ አንድ ጥግ እንዲሰበሰብ ካደረ በኋላ በአንድ መስመር አስቁመው መጠበቅ ጀመሩ፡፡ጥቂት ቆይቶ ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ፣የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎቹ ናትናኤል ፈለቀና አጥናፉ ብርሃነ እጃቸውን በሰንሰለት እንደታሰሩ በሌላ ጉዳይ ከታሰሩ እስረኞች ተጣምረው መሣሪያ በታጠቁ ፖሊሶች ታጅበው ወደ ውስጥ ገቡ፡፡ ጉዳዩ ከሚታይበት ችሎት ፊት ለፊት ባለው በረንዳ ላይ እንዲቆሙ ከተደረጉ በኋላ ሰንሰለታቸውን ተፈቶ እንዲቀመጡ ተደረገ፡፡በዕድሜ ገፋ ያሉት የችሎት አስተባባሪ ግቢ ውስጥ ተሰብስቦ ወደ ቆመው ሕዝብ ቀረብ ብለው፤ በችሎቱ የመያዝ አቅም ልክ ሰዎች ለማስገባት እንደታሰበ በመግለጽ የተወሰነ ሰው እንዲሰለፍ ጠየቁ፡፡ ነገር ግን በርከት ያለ ሰው ለመግባት ፍላጎት በማሳየቱ ተጠርጣሪዎቹ የሚፈልጉትን ሰው መርጠው እንዲያስገቡ ዕድል ይሰጣቸው የሚለው ሐሳብ ጸንቶ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ የሦስት ሰው እንዲሰጥ ተደረገ፡፡ በዚህም ምክንያት ቤተሰብና ጓደኛ ችሎቱን ተቀላቀለ፡፡ዛሬ ችሎት ውስጥ ለመግባት ዕድል ካገኙት መካከል አንዷ ነበርኩና የችሎቱን ሪፖርት እንዲህ ጻፍኩት፡፡ ችሎቱ ተሰየመ 
መዝገብ አንድ
ወጣቱ ዳኛ ችሎቱ ላይ ከተሰየሙ በኋላ ‘በእነ አጥናፉ መዝገብ' ሲሉ ሦስቱ ተጠርጣሪዎች እንዲቀርቡ አዘዙ፡፡የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ መምሪያ ሁለት ፖሊሶች ተጠርጣሪዎቹን ይዘው ችሎት ፊት ቀረቡ፡፡ አቶ አመሐ መኮንን ለአጥናፉ ብርሃነ እና ለናትናኤል ፈለቀ፣ ዶክተር ያሬድ ለገሰ ደግሞ ለኤዶም ካሳዬ ጠበቃ ኾነው ተሰየሙ፡፡ ዳኛው መዝገቡን ገለጥ አድርገው ከተመለከቱ በኋላ፤ ‹‹ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው ፖሊስ በተሰጠው የዐስር ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ምርመራው አጠናቆ የደረሰበትን ድምዳሜ ለችሎት እንዲያሳውቅ የነበረ ቢኾንም ፖሊስ በዛሬው ዕለት አንድ ማመልከቻ በጹሑፍ ይዞ ቀርቧል፡፡ ይህን ማመልከቻም በንባብ አሰማለሁ›› በማለት የፖሊስን ማመልከቻ ማንበብ ጀመሩ፡፡

‹‹
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በወንጀል በሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 59/2 መሰረት የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቀን በምርመራ ላይ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ተጠርጣሪዎች ሚስጥራዊ በኾነ መንገድ በሕቡዕ በመደራጀት በሕጋዊ መንገድ ሥልጣን የያዘውን መንግሥት በሕገ ወጥ መንገድ ከሥልጣን ለማውረድ በማሰብ፣ ይህንንም ሐሳብ በውጭ አገር ከሚገኙ አሸባሪ ድርጅቶች ጋራ በመስማማትና አገሪቱን ለማተራመስ ትእዛዝ በመቀበል፣ትእዛዙን ለማሳካት የሚያስችላቸውን ገንዘብ በመቀበል፣እንዲሁም ስልጠና በመውሰድ በአገሪቱ ላይ ብጥብጥ ለማነሳሳትና ብጥብጡንም ለመምራት በመንቀሳቀስ የሽብር ተግባር ፈፅመዋል፡፡
በመኾኑም ይህን የሽብር ተግባር ለማጣራት እንዲረዳን በፀረ ሽብር ዐዋጁ ቁጥር 652/2001 አንቀፅ 28 መሰረት ተጨማሪ 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠን እንጠይቃለን›› በማለት ማመልከቻውን በንባብ ካሰሙ በኋላ ጠበቆች በማመልከቻው ላይ የሚሉት ነገር ካለ በሚል ጠየቁ፡፡


ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን ‹‹በሚገባ የምንለው ነገር አለ ክቡር ፍርድ ቤት›› ካሉ በኋላ ‹‹ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ካዋለ ሃያ ሦስት ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህን ጊዜ ውስጥም ሁለት ጊዜ በችሎት አቅርቧቸዋል፡፡ በቀረቡበት ጊዜም ለጥርጣሬዬ ዋና ምክንያት ነው ያለው ተጠርጣሪዎች በማኅበራዊ ድረ-ገፅ ላይ በጻፉት ጹሑፍ በሚል እንጂ አንድም ጊዜ የሽብር ተግባር በመፈፀማቸው ነው ሲል አልተሰማም፡፡ ጉዳዩን ከሽብር አንጻር እየመረመረው እንደኾነም ገልፆ አያውቅም፡፡ ፍርድ ቤቱ ከመዝገቡ መረዳት እንደሚችለው ከዚህ በፊት በመደበኛው የወንጀል ሕግ የጊዜ ቀጠሮ ሥነ ሥርዓት አጠያየቅ መሠረት ዐሥራ አምስት ቀን ጠይቆ ዐሥር ቀን ተፈቅዶለታል፡፡ እንዲሁም የሽብር ዐዋጁን አንቀፅ ጠቅሶ አያውቅም፡፡ፖሊስ በውጭ አገር ከሚገኝ አሸባሪ ድርጅት ጋር ከማለት በስተቀር የትኛው ድርጅት የሚለውን በስም እንኳን አልጠቀሰም፡፡ አሁን ከተጠርጣሪዎቹ በኩል ያለው መረጃ አለን ሁለቱንም ተጠርጣሪዎች ለአንድ ግዜም ቢኾ አግኝቼ አነጋግሬያቸዋለሁ፡፡እነሱም ስለተደረገላቸው ምርመራ ሲነግሩኝ በጥያቄም ቢኾን ስለሽብር ተግባር ወይም ደግሞ አሸባሪ ስለሚባል ድርጅት የተጠየቁት አንድም ጥያቄ የለም የመለሱትም ነገር የለም፡፡ ሥልጠና ወሰዳችሁ የተባለውንም በሚመለከት ስልጠና የወሰዱት ‹‹አርቲክል 19›› እና ‹‹ፍሪደም ሀውስ›› ከተባሉ ድርጅቶች ነው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ደግሞ ከአሜሪካና ከእንግሊዝ መንግሥስት እውቅና የተሰጣቸው ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ የሚሠሩ ዓለም አቀፍ ሕጋዊ ድርጅቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ድርጅቶች በኢትዮጵያም ቢኾን አሸባሪ ድርጅቶች ተብለው አልተፈረጁም፡፡››በማለት መከራከሪያቸውን አቀረቡ፡፡
አያይዘውም ‹‹ፖሊስ ለዛሬ ቀጠሮ እንዲሰጠው ሲጠይቅ የሰጠው ምክንያት፤ የምስክሮችን ቃል መቀበል ይቀረናል የሚል ነበር፡፡ የስንት ምስክር ቃል ተቀበሉ? ያልተያዙ ግብረአበሮቻቸውን መያዝ ይቀረናል ብለውም ነበር፣ መቼ ግብረአበር ያዙ? ሰነድ ማስተርጎም ይቀረናል ብለው ነበር፡፡ሰነድ ለመተርጎም እንዴት ይህን ያህል ጊዜ ይፈጃል? ቢፈጅስ በሰነድ መተርጎም ምክንያት ተጠርጣሪዎቹን አስሮ ማስቀመጥ ለምን ያስፈልጋል?፣ ተጠርጣሪዎቹን ቃል መቀበል ይቀረናል ብለው ነበር የስንት ምስክር ቃል ተቀበሉ? እንዲሁ በደፈናው በሽብር ጉዳይ ጠርጥረናቸዋል በማለት የሽብር ዐዋጁን መንፈስ ወደ ተፈለገው ጉዳይ በመቀልበስ በመደበኛው የወንጀል ሕግ ሊታይ የሚገባውን ጉዳይ ከሽብር ጋር ማያያዝ ተገቢ ያልሆነና ለማንም የማይጠቅም ጉዳይ ነው፡፡›› በማለት ተቃውሞአቸውን ገለጹ፡፡
በመጨረሻም፤ ‹‹ይህ በደንበኞቼ ላይ የቀረበ አግባብ ያልሆነ አካሄድ በመኾኑ ፍርድ ቤቱም ቀደም ብሎ የተያያዘውን የምርመራ መዝገብ በመርመር ጉዳዩ በሽብር ዐዋጁ መሰረት ሊታይ አይገባም በሚል ትእዛዝ እንዲሰጥልና ተጠርጣሪዎቹን ሊያቀርባቸው የሚችል ዋስ አስጠርቶ በዋስ እንዲለቀቁ ትእዛዝ ይስጥልን፡፡›› በማለት ለችሎት አመለከቱ፡፡
የኤዶም ካሳዬ ጠበቃ ዶ/ር ያሬድ ለገሰ በበኩላቸው፤‹‹የሥራ ባልደረባዬ ያሉት በሙሉ እኔም የምስማማበት ኾኖ እንዲመዘገብልኝ እጠይቃለሁ፡፡ በተጨማሪም ፖሊስ የምርመራ ጉዳዩ የሽብር ተግባር ነው ከማለት ውጪ ምክንያታዊ ጥርጣሬ ያለ መኾኑን እንኳን አላስረዳም፡፡ ደንበኛዬ ሥልጠና አግኝተዋል የተባሉት ድርጅቶችም ቢኾኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁና በኢትዮጵያም ሽብርተኛ ተብለው ያልተፈረጁ ድርጅቶች ናቸው፡፡ የተጠቀሰውና በምርመራ ላይ ነው የተባለው ጉዳይ በመደበኛ ኹኔታ ሊታይ የሚችል በመኾኑ የዋስትና መብታቸው ተከብሮላቸው በዋስ እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ይስጥልን፡፡›› ብለው ጠየቁ፡፡
ሁለቱ ጠበቆች አስተያየታቸውን እንዳጠናቀቁ ዕድል እንዲሰጠው በጠበቃው አማካንነት ጥያቄ ያቀረበው አጥናፉ ብርሃነ፤‹‹እኔ ለፍርድ ቤቱ የማመለክተው ነገር አለ፡፡ እስር ቤት ውስጥ እንግልት እየደረሰብኝ ነው፡፡ለሊት ሳይቀር እየተጠራሁ እመረመራለሁ፡፡ ድብደባ ደርሶብኛል፡፡ ዛቻና ማስፈራራት እየደረሰብኝ ነው፡፡ ከጠበቃና ከቤተሰብ ጋራ አንዴ ብቻ ነው የተገናኘሁት፡፡በአያያዜ ላይ ሰብዓዊ መብቴ ተጥሷ›› በማለት አመለከተ፡፡

በቀረበው የዋስትና ጥያቄ ላይ ፖሊስ አስተያየት ካለው እንዲናገር እድል ሰጡ፡፡ ፖሊስ በበኩሉ ‹‹ጉዳዩ ወደ ሽብር እንዲያመራ ያደረገው ምርመራችን ነው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ድርጊቱን የፈፀሙት በቡድን ኾነው በሕቡዕ ተደራጅተው ነው፡፡ በድብቅ ተደራጅቶ ቅስቀሳ ማድረግ ደግሞ በሽብር ሕጉ መሰረት ወንጀል ነው፡፡›› በማለት ማብራሪያ ሰጡ፡፡
‹‹ሕጋዊ ድርጅት ነው የተባለው ‹አርቲክል 19›ም በኢትዮጵያ ሕጋዊ ኾኖ አልተመዘገበም፡፡ እንዲሁም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋርም ተገናኝተዋል›› በማለትም ምላሽ ሰጡ፡፡
አያይዘውም፤‹‹አጥናፉ ብርሃነ መሥሪያ ቤታችንን ሊወክል የማይችል ነገር ተናግሯል፡፡ እንደ ፖሊስ ተቋም ምርመራ ተደርጓል ተደብድቤያለሁ ያለው ግን ውሸት ነው›› በማለት አስተባብሏል

ዳኛው በበኩላቸው ‹‹እስካሁን በምርመራ አቆይታችሁ ምን ሠራችሁ?›› በማለት የማጣሪያ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ‹‹የማስረጃ ትርጉም በሚመለከት ፖሊስ የራሱ ትርጉም ቤት የለውም በሕጋዊ ትርጉም ቤት ወስዶ ነው የሚያስተረጉመው እንደሱ ለማድረግ በሂደት ላይ ነው፣ የምስክሮችን ቃል መቀበል በሚመለከትም፣ በውጭ ያሉት የተጠርጣሪዎቹ ግብረአበሮች ምስክሮችን እያስፈራሩብን በመሆኑ የምስክሮችን ቃል መቀበል አልቻልንም›› በማለት መልስ ሲሰጡ ዳኛው አቋረጧቸውና፤‹‹ፖሊስ ምስክሮችን ቃል መቀበል ከፈለገ ይችላል፡፡ አልቀርብም ቢሉ እንኳን በመጥሪያ አስራችሁ መቀበል አትችሉም?›› ሲሉ ለፖሊስ ጥያቄ አቀረቡ፡፡

‹‹ግብረአበሮቹ የምስክሮቹን አድራሻ እያስቀየሩብን ተቸገርን፡፡ ለዚሁ ተግባር ገንዘብ እየተላከላቸው ነው›› ሲሉ መልስ ሰጡ፡፡ አያይዘውም ፤‹‹በተጨማሪም ድርጊቱን የፈጸሙት ተደራጅተው በመኾኑ ኢሜሎቻቸውን በፓስወርድ የመቆለፍ ነገር ገጥሞናል፡፡ እርሱንም መመርመር ይቀረናል፡፡›› በማለት ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮው እንዲፈቀድላቸው ጠየቁ፡፡
ዳኛው የማጠቃለያ ሐሳብ እንዲያቀርቡ መልሰው ለጠበቆች ዕድል ሰጡ፤አቶ አመሐም የሚከተለውን አስተያየት ሰጡ፤‹‹የተከበረው ፍርድ ቤት ፓሊስ አሁንም ቢኾን የተለየ የገለጸው ነገር የለም ቅድም ያለውን ነው የደገመው፤ተጠርጣሪዎቹን ሲይዝም ኾነ የጊዜ ቀጠሮ ሲጠይቅ ድረ ገጽ ላይ መጻፍን ጠቅሶ ነው የድርጊቱ ሽብር መኾን ዛሬ አይደለም ሊከሰትለት የሚገባው ቀደም ሲል ይህ እምነት አልነበረም፤አሁንም ቢኾን በሽብርተኝነት ለመጠርጠር የሚያበቃ አዲስ የተገኘ ነገር የለም፡፡ እንዲሁ ስናስበው ድርጊቱ የሽብር ተግባር መስሎናል በሚል ምክንያት ተጠርጣሪዎቹን አስሮ ማቆየት ዐዋጁ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ እንዲውል ማድረግ›› በማለት ደንበኞቻቸው በዋስ እንዲፈቱ አጥብቀው ተከራከሩ፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ሲያዳምጡ የቆዩት ዳኛ በመጨረሻም ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ‹‹ፖሊስ ከሽብር ጋር በተያያዘ ለጥርጣሬ የሚያበቃ በቂ ምክንያት አለኝ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ካለ፤የምርመራ ጊዜ ሊሰጠው ይገባል በዚህም መሠረት የጠየቀው ሃያ ስምንት ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተፈቅዶለታል›› በማለት መዝገቡን ለሰኔ 7 ቀን 2006 ዓ.ም ጠዋት ቀጠሮ ሰጡ፡፡

መዝገብ ሁለት
ሦስቱ ተጠርጣሪዎች ከእነ አጃቢዎቻቸው ችሎቱን ለቀው እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ ‹‹እነ ዘላለም›› ሲሉ ዳኛው ተጠርጣሪዎቹ እንዲቀርቡ ጠየቁ አንድ ፖሊስ ወደ ችሎቱ ገብቶ በመንገድ ላይ መኾናቸውን በመግለጽ እስኪመጡ ፍርድ ቤቱ ሌላ መዝገብ እየተመለከተ እንዲቆይ ጠየቀ፡፡በሌላ ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ ኹለት መዝገቦች ከታዩ በኋላ መምጣታቸው ተነግሮ በድጋሚ እንዲቀርቡ ታዘዘ፡፡ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስና የሕግ መምሕርና የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ዘለዓለም ክብረት በፖሊስ ታጅበው ወደ ችሎቱ ገቡ፡፡
ዳኛው በድጋሚ አሰየሙ፡፡ ጠበቃው አመሐ መኮንን ለሦስቱም ተጠርጣሪዎች የቆሙ መኾናቸውን ተናግረው አስመዘገቡ፡፡ ፖሊስ የሁለተኛውን መዝገብ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ ቀለል በማድረግ፤‹‹የተጠርጣሪዎቹን ቃል ተቀብለናል ምርመራ ግን ይቀረናል›› በማለት ቀለል አድርጎ አቀረበ፡፡ ‹‹ምን ዓይነት ምርመራ ነው የቀራችሁ?›› በማለት ዳኛው ጠየቁ፡፡ ጉዳዩ ቀድሞ ከቀረበው ጋር አንድ መኾኑንና ማመልከቻ ከመዝገቡ ጋር ማያያያዙን ፖሊስ ተናገረ፡፡ ዳኛው ማመልከቻው ገልጠው ሲያነቡት ከቀድሞው ጋር አንድ ዓይነት ነበር፡፡
ጠበቃው አቶ አመሐም በበኩላቸው አብዛኛው አስተያየት ከቀድሞው ጋር አንድ ዓይነት መኾኑን ከገለጹ በኋላ የቀረቡት ተጠርጣሪዎቹ ቀደም ሲል የተባለውን ስላልሰሙና ግልፅ እንዲሆንላቸው ለማድረግ ነው በማለት በእነ አጥናፉ መዝገብ ያቀረቡትን መቃወሚያ ደገሙት፡፡ አያይዘውም፤‹‹አሁንም ግን በተደጋጋሚ የምናመለክተው እነዚህ ልጆች በይፋ አሸባሪ ከተባለ ድርጅት ጋር ተገናኛችሁ አልተባሉም አርቲክል 19ኝም ቢኾን እዚህ አገር ከመንግሥት ጋር ሳይቀር የሚሠራ ድርጅት ነው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ላይ ሲመጣ አሸባሪ ካልተባለ፤እነዚህ ልጆች ገጽ ከፍተው በስማቸው ከነፎቶአቸው ፊት ለፊት የሚጽፉ ልጆች ናቸው በሕቡዕ ተደራጅታችኋል ሊባሉ አይገባም፡፡ ገንዘብ ተቀብለዋል ለተባውም በምርመራ ወቅት በራሳቸው አንደበት መቼ? የትና? እንዴት?ለምን ዓይነት ተግባር እንደተቀበሉ በግልጽ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ደግሞ ተስፋዓለም እና አስማማው ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ የዞን ዘጠኝ አባልም አይደሉም፡፡በምርመራ ወቅት ወደ ሽብር ተግባር ሊያመራ የሚችል ምንም ዓይነት የቀረበባቸው ጥያቄና መልስም የለም፡፡ ፍርድ ቤቱም ይህንን ተገንዝቦ የዋስትና ጥያቄያችንን እንዲቀበለን እንደጠይቃለን›› በማለት ደንበኞቻቸው በዋስ እንዲፈቱ አመለከቱ፡፡
ፖሊስ በበኩሉ ድርጊቱ የተፈፀመው በቡድን በመኾኑ ስማቸው የተጠቀሱት ተጠርጣሪዎች ለድርጊቱ አስተዋፆ ያላቸው መኾኑን ጠቅሶ የዋስ መብት ጥያቄውን በመቃወም በማመልከቻው የጠየቀው የሃያ ስምንት ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠየቀ፡፡
ዳኛው የምርመራ መዝገቡን እየተመለከቱ ‹‹ከሚያዚያ 18 በኋላ ምርመራ ስለማድረጋችሁ መዝገቡ አያሳይም ምን ስታደርጉ ነው የቆያችሁት?›› ካሉ በኋላ ወደ ተጠርጣሪዎቹ ዞር ብለው ‹‹እናንተ መቼ ለመጨረሻ ጊዜ ምርመራ የተደረገላችሁ?›› በማለት ጠየቁ፡፡ የአዲስ ጉዳዩ አስማማው፤‹‹ባለፈው ሳምንት በእኔ በኩል በፖሊስ ምንም ዓይነት ድብደባ ባይፈጸምብኝም ከተያዝኩበት ቀን ጀምሮ የዞን ዘጠኝ አባል ነህ /አይደለህም የሚል ጥያቄ ብቻ ነው እየተጠየኩ ያለሁት፡፡ አይደለሁም ብልም የሚሰማኝ የለም ከፍተኛ የኾነ የሥነ ልቦና ተጽኖ እየደረሰብኝ ነው…›› አስማማው ሲናገር እንባው ላለማርገፍ አንገቱን ወደ ሰማይ ቀና እያደረገ ለመናገር ቢሞክርም ድምፁ ቀስ እያለ በሲቃ እየተዋጠ ሄደና የብሶት እንባውን ዘረገፈው፡፡ ‹‹ይቅርታ ክቡር ፍርድ ቤት…የሠራሁት ወንጀል ካለ ይነገረኝ ብልም የሚነግረኝ የለም›› ቤተሰቦቹን ጨምሮ ችሎት የነበረው አብዛኛው ታዳሚ ድምጽ በሌለው ለቅሶ እንባውን አፈሰሰ፡፡ችሎቱ ለደቂቃ በጸጥታ ተዋጠ፡፡
ጠበቃው አቶ አመሐ፤‹‹የተከበረው ፍርድ ቤት አሁንም ሃያ ስምንት ቀናት ቢሰጣቸው ይጨርሱታል ወይ የሚለው ላይ ትኩረት ይሰጥልን ምንድነው የሚመረመረው የሚለውን በሚመለከት ፖሊስ ምንም ያለው ነገር የለም እርሱንም ያብራራልን›› በማለት አመለከቱ፡፡ የ‹‹እስካሁን ምንድነው የሠራችሁት?›› ዳኛው መልሰው ፖሊሱን ጠየቁ፤‹‹የተከበረው ፍርድ ቤት ኢሜላቸውን እየመረመርን ነው፡፡ ለማሰራጨት ያሰቡትን ለአመጽ መቀስቀሻ የሚኾነውን ጹሑፍ ከኢሜላቸው ላይ እየመረመርን ነው፡፡ ኢሜል ሲባል ብቻውን አይደለም ትዊተር አለ፣ወርድ ፕሬስ የሚሉት አለ ብዙ ናቸው የሚጠብቀን ምርመራ ቀላል አይደለም››በማለት መልስ ሰጡ፡፡

ፖሊስ እስካሁን ኢሜላቸውን መርምሮ ለምን እንዳልጨረሰ ከዳኛው ሲጠየቅ ‹‹ዳታ ክፍላችን ውስጥ ያለን ኮምፒዩተር አንድ ብቻ ስለኾነ የሚደርሰን በወረፋ ነው ስለዚህ ጊዜ ይፈጃል›› በማለት መልስ ሰጡ፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ሲያዳምጡ የቆዩት ዳኛ በዚህኛውም መዝገብ ‹‹ፖሊስ ከሽብር ጋር በተያያዘ ለጥርጣሬ የሚያበቃ በቂ ምክንያት አለኝ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ካለ፤የምርመራ ጊዜ ሊሰጠው ይገባል በዚህም መሠረት የጠየቀው ሃያ ስምንት ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተፈቅዶለታል›› በማለት ለሰኔ 7 ቀን 2006 ዓ.ም ጠዋት ቀጠሮ ሰጡ፡፡ተጠርጣሪዎቹም አንገታቸውን እንደ ደፉ ችሎቱን ለቀው ወጡ፡፡ 
ምንጭ ዞን9 

No comments:

Post a Comment