Friday, October 4, 2013

ግንቦት ሰባት ከግብጽ መንግስት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው አስታወቀ።


ይህንን ያስታወቁት የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እሁድ መስከረም አስራዘጠኝ ሁለትሺህ ስድስት በስዊድን ዋና ከተማ የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሃይል ከአባላቶቹ እና ደጋፊዎቹ ጋር ባካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ያለው የህውሃት መንግስት እገነባለሁ ስለሚለው የአባይ ወንዝ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ የተነሳ የግብጽ መንግስት ኢትዮጵያውያን ተቃዋሚዎች ድርጅቶችን ያስታጥቃል እናንተስ
የዚህ ተጠቃሚ ናችሁ ወይ በሚል ለቀርበላቸው ጥያቄ  በሰጡት መልስ ነው። ይህ በርካታ ቁጥር ያላቸው በስቶክሆልም እና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተገኙበት ህዝባዊ ስብሰባ የተጀመረው በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ በስምንት ሰዓት ላይ ሲሆን ስብሰባውን የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ከአሜሪካን አገር በስካይፒ በመክፈ ሲናገሩ የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሃይል ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ጨቋኝ እና አፋኝ ስርዓት ለማስለወጥ ያሉት ሰላማዊና ሌሎች መሰል ትግሎች ላለፉት 22 ዓመታ ተሞክረው ምንም ውጤት ማምጣት አለመቻሉን በመጠቆም ድርጅታቸው እና ሌሎች ይህ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ የመጣው ገደብ ያጣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የህግ ልዕልና አለመከበር ያስመረራቸው መሰል ዴሞክራሲያዊ  ድርጅቶች ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ተጨባጭ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ለማምጣት የትጥቅ ትግል መጀመራቸውን አስገንዝበዋል። ሊቀመንበሩ ከዚህ በተጨማሪም ይህ ፈታኝ እና እልህ አስጨራሽ የሆነውን ትግል ከግቡ ለማድረስ የሚጠይቀውን ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል የህዝባዊ ሃይሉ ዓመራር እና አባላት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በመዘጋጀት ላይ ላይ መሆናቸውን በማስረዳት ጊዜው በተለያዩ ኢምንታዊ ጉዳዮች ላይ የሚደረውን ጉንጭ አልፋ ክርክር ወደ ኋላ በመተው ቀበቶን ጠበቅ በማድረግ ሁሉም የገዥው ፓርቲ ጭቆና እና በደል ያስመረረው ኢትዮጵያዊ በሙያው፡በገንዘቡ፡በችሎታው እና በተለያየ መልኩ በማገዝ የትግሉን ጎራ እንዲቀላቀል ጥሪያቸውን አቅርበዋል። ከዛም በመቀጠል ዋና ጸሃፊው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሃይልን ዓላማዎች፡ተልዕኮዎች እና ራዕይ በማስተዋወቅ ህዝባዊ ሃይሉ ከምስረታ ጀምሮ አሁን ያለበትን ደረጃ ያለበትን በምስልና በጽሁፍ የተደገፈ ገለጻ ለተሰብሳቢው አቅርበዋል። እሳቸው እና ሌሎች የአመራር አካላት እንዲሁም አባላት የተገኙበት የውትድርና ስልጠና አንዱ የበታች አንዱ የበላይ እንዳልሆነ በማስገንዘብ ይህ ህዝባዊ ሃይል ቤተሰባቸውን፡ስራቸውን፡ንብረታቸውን፡ እና የተደላደለ ኑሯቸውን
በመተው ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን የተዋቀረ እንደሆነ ገልጸዋል። ይህ ህዝባዊ ሃይል በአገር ውስጥ ትግራይን ጨምሮ ከአፋር፡ ከአማራ እና ከጋምቤላ አካባቢዎች የመጡና የገዥው ጨቋኝ እና አፋኝ ስርዓት ያንገሸገሻቸው በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ በማስረዳት በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ለማምጣትና የህግ የበላይነት እንዲከበር ለመታገል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በቁርጠኝነት መዘጋጀታቸውን በእለቱ በአቶ  አንዳርጋቸው ከቀረበው ስእላዊ ዘገባ ለመረዳት ተችሏል። የግንቦት ሰባት ዓላማ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ማስፈን ብቻ ሳይሆን ባለፉት 22 ዓመታት ኢትዮጵያውያን የተገፈፉትን ክብራቸውን ማስመለስ ጭምር መሆኑን አቶ አንዳርጋቸው አስምረውበታል። የህውሃት መንግስት በኢትዮጵያውያን ላይ የሚያደርሰው በደል እና ህገወጥ ድርጊት አድማሱን እያሰፋ ዛሬ የሃይማኖት ተቋማትን ማካተቱን አቶ አንዳርጋቸው ጠቁመው ለእዚህም እንደዓብነት በዋልድባ ገዳም መነኮሳት ላይ በገዥው ፓርቲ ሎሌዎች የተፈጸመባቸውን እጅግ አሳፋሪ እና ኢሰብዓዊ ድርጊት ጠቅሰዋል። ከእረፍት በኋላ በቀጠለው የጥያቄ እና መልስ ዝግጅት ላይ ተሰብሳቢው ለድርጅቱ ጸሃፊ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ከተነሱት ጥያቂዎች መካከል ድርጅታቸው ከ ኦሮሞ ነጻ አውጭ ድርጅት ጋር ስለነበረው ውህደት፡ ስለ አባይ ግድብ እና የግብጽ መንግስት ሚና፡ ከትግሉ ስኬት በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚቋቋመው መንግስት እንዲሁም የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሃይል ከሌሎች የትጥቅ ትግል ካነገቡ የተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ስላለው ግንኙነት ይገኙበታል። አቶ አንዳርጋቸው በሰጡት መልስ ሊገነባ የታሰበው የአባይ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ የግንባታው ቦታን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ድርጅታቸው እንደማይስማማ በማስረዳት በተለይም የዚህ መጠነ ሰፊ ፕሮጀክት ዓላም የኢትዮጵያን ህዝብ የኤሌክትሪክ ብርሃን ተጠቃሚ ማድረግ ሳይሆን ኤሌክትሪክ ለጎረቤት ሃገራት በመሸጥ የሚገኘውን በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገቢ በሙስና ለተዘፈቁ የገዥው ፓርቲ መሪዎችን እና ሎሌዎቻቸውን ኪስ ለማድለብ የታቀደ መሆኑን አስታውቀዋል። ከዛም በመቀጠል በጀነራል ከማል ገልቹ ከሚመራው የኦነግ ቡድን ጋር ግንቦት ሰባት ለመፍጠር ተጀምሮ የነበው ውጥን በተለያዩ ውስጣዊ ምክንቶች የተነሳ እንደታሰው ሊሳካ አለመቻሉን አቶ አንዳርጋቸው አስረድተው ሆኖም ግን ይህንን ውጥን እንደገና ለመቀጠል አሁንም ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች በሁለቱም ወገኖች በኩል እንዳሉ ገልጸዋል።
ድርጅታቸው የትጥቅ ትግል የሚያኪያሂደው ስልጣን ለመያዝ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤት እንዲሆን ለማስቻል ሁኔታዎችን ማመቻቸት መሆኑን ጠቁመው ከሌሎች የትጥቅ ትግል ያነገቡ ተቃዋሚ ድርጅቶች ማለትም ከትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከአፋር ከጋምቤላ እና ከሌሎችም አካባቢዎች የተውጣጡ ድጅቶች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን የግንቦት ሰባት ጸሃፊ ለተሰብሳቢው አስረድተዋል። ወደብ የማስመለስን ጉዳይ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ሲመልሱም ይሄ ጉዳይ ሊፈታ የሚችለው ኢትዮጵያ ውስጥ በህዝብ የተመረጠ መንግስት አማካኝነት እንደሆነ የግንቦት ሰባት አቋም መሆኑን በማስረዳት ድርጅታቸው የኢትዮጵያንና የኤርትራን ህዝቦች በማቀራረብ እና ከተቻለም ዲሞክራሲያዊ እና መከባበር በተሞላበት መንገድ እንደገና በማዋሃድ እንደሚያምን ለኤርትራ ህዝብ ከማንም በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ወዳጁ እንደሆነ ከአቶ አንዳርጋቸው መልስ ለመረዳት ተችሏል። በመጨረሻም የአንድነት ለዲሞክራሲ እና ፍትህ ፓርቲ እሁድ እለት በአዲስ አበባ ሊያደርግ የነበረው ሰላማዊ ተቃውሞ  በህውሃት የጸጥታ ሃይሎች ግፊት እንዳይካሄድ መደረጉ ምን ያህል በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ እንዳለ የሚያሳይ መሆኑን በመጠቆም አቶ አንዳርጋቸው የአንድነት ፓርቲ እና አባላቱ ያሳዩትን ጥረት በማድነቅ  ድርጅታቸው በዚህ አጋጣሚ ያለውን የትግል አጋርነት አስተላልፈዋል። በእለቱ በገዥው የአምባገነን ስርዓት ምክንያት እንዲሁም በተለያዩ የዓለማት ክፍላት ግድያን፡እስራትን እና ድህነትን በመሸሽ ህይወታቸውን ላጡ በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖች የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት የተደረገ ሲሆን የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖት ተወካዮችም ንግግር አሰምተዋል። ህዝባዊ ስብሰባው እንደኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ አስራሁለት ሰዓት ላይ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።  


No comments:

Post a Comment